መዝሙር 72:1-20

መዝሙር 72:1-20 NASV

እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍትሕን ለንጉሥ፣ ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ ዐድል፤ እርሱም ሕዝብህን በጽድቅ ይዳኛል፤ ለተቸገሩትም በትክክል ይፈርዳል። ተራሮች ብልጽግናን፣ ኰረብቶችም የጽድቅን ፍሬ ለሕዝቡ ያመጣሉ። ለተቸገረው ሕዝብ ይሟገታል፤ የድኾችን ልጆች ያድናል፤ ጨቋኙንም ያደቅቀዋል። ፀሓይ እስካለች ድረስ፣ ጨረቃም በምትኖርበት ዘመን ሁሉ፣ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። እንደ ዝናብ በታጨደ መስክ ላይ ይወርዳል፤ እንደ ካፊያም ምድርን ያረሰርሳል። በዘመኑ ጽድቅ ይሰፍናል፤ ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም ሰላም ይበዛል። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ ከታላቁም ወንዝ እስከ ምድር ዳርቻ ይገዛል። የበረሓ ዘላኖች በፊቱ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም ዐፈር ይልሳሉ። የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት፣ ግብር ያመጡለታል፤ የዐረብና የሳባ ነገሥታት፣ እጅ መንሻ ያቀርባሉ። ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ይገዙለታል። ድኻው በጮኸ ጊዜ፣ ችግረኛውና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ድኾችንም ከሞት ያድናል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል፤ ደማቸውም በርሱ ፊት ክቡር ነው። ዕድሜው ይርዘም! ወርቅም ከሳባ ይምጣለት፤ ዘወትር ይጸልዩለት፤ ቀኑንም ሙሉ ይባርኩት። በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ። ፍሬው እንደ ሊባኖስ ይንዠርገግ፤ በከተማ ያለውም እንደ ሜዳ ሣር እጅብ ብሎ ይውጣ። ስሙ ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ ዝናው ፀሓይ የምትኖረውን ዘመን ያህል ይዝለቅ። ሕዝቦች ሁሉ በርሱ ይባረኩ፤ ሕዝቡ ሁሉ ቡሩክ ነህ ይበለው። ብቻውን ድንቅ ነገር የሚያደርግ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። ክቡር ስሙ ለዘላለም ይባረክ፤ ምድርም ሁሉ በክብሩ ትሞላ። አሜን፤ አሜን። የእሴይ ልጅ የዳዊት ጸሎት እዚህ ላይ ተፈጸመ።