ዮሐንስ 21:4-14
ዮሐንስ 21:4-14 NASV
ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር። እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የለንም” አሉት። እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወድደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ እኮ ነው!” የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘልሎ ወደ ባሕሩ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ። ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስኪ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ ዐምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደ ሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ እንዲሁም ዓሣውን ሰጣቸው። እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

