ጽዮን ግን፣ “እግዚአብሔር ትቶኛል፤ ጌታም ረስቶኛል” አለች። “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን? ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን አልረሳሽም! እነሆ፤ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ፤ ቅጥሮችሽ ምን ጊዜም በፊቴ ናቸው። ወንዶች ልጆችሽ ፈጥነው ይመለሳሉ፤ ያፈራረሱሽም ከአንቺ ይሸሻሉ። ዐይንሽን ቀና አድርጊ፤ ዙሪያውንም ተመልከቺ፤ ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝ፤ እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤ እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊያቸዋለሽ” ይላል እግዚአብሔር። “ፈራርሰሽ ባድማ ብትሆኚ፣ ምድርሽ ፈጽሞ ቢጠፋ፣ ዛሬ ለሕዝብሽ ጠባብ ብትሆኚም እንኳ፣ የዋጡሽ ከአንቺ ይርቃሉ። በሐዘንሽ ዘመን የወለድሻቸው ልጆች፣ ጆሮሽ እየሰማ፣ ‘ይህ ቦታ በጣም ጠብቦናል፤ የምንኖርበት በቂ ስፍራ ስጪን’ ይሉሻል። በልብሽም እንዲህ ትያለሽ፣ ‘እነዚህን የወለደልኝ ማን ነው? እኔ ሐዘንተኛና መካን፣ የተሰደድሁና የተጠላሁ ነበርሁ፤ እነዚህን ማን አሳደጋቸው? ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ ታዲያ፣ እነዚህ ከየት መጡ?’ ” ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ አሕዛብን በጥቅሻ እጣራለሁ፤ ዐርማዬንም ለሕዝቦች ከፍ አደርጋለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽን በዕቅፋቸው ያመጡልሻል፤ ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ይሸከሙልሻል። ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ፣ እቴጌዎቻቸው ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዱልሻል፤ የእግርሽን ትቢያ ይልሳሉ፤ አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፤ እኔን ተስፋ የሚያደርጉም አያፍሩም።” ከተዋጊ ብዝበዛ ማስጣል፣ ከጨካኝስ ምርኮኞችን ማዳን ይቻላልን? እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤ “ከተዋጊዎች ላይ ምርኮኞች በርግጥ ይወሰዳሉ፤ ከጨካኞችም ላይ ምርኮ ይበዘበዛል፤ ከአንቺ ጋራ የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፤ ልጆችሽንም እታደጋለሁ። አስጨናቂዎችሽ የራሳቸውን ሥጋ እንዲበሉ አደርጋቸዋለሁ፤ በወይን ጠጅ እንደሚሰከር ሁሉ፣ በገዛ ደማቸው ይሰክራሉ። ከዚያም የሰው ዘር ሁሉ፣ እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽ፣ ታዳጊሽም የያዕቆብ ኀያል እንደ ሆንሁ ያውቃል።”
ኢሳይያስ 49 ያንብቡ
ያዳምጡ ኢሳይያስ 49
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኢሳይያስ 49:14-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች