እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፤ እረዳህማለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። እነሆ፥ የሚቃወሙህ ሁሉ ያፍራሉ፤ ይዋረዱማል፤ እንዳልነበሩም ይሆናሉ፤ ጠላቶችህም ይጠፋሉ። የሚያሠቃዩህንም ሰዎች ትሻቸዋለህ፤ አታገኛቸውምም፤ እንዳልነበሩ ይሆናሉና፤ የሚዋጋህም የለም። ቀኝ እጅህን የያዝሁህ፥ እንዲህም የምልህ እኔ አምላክህ ነኝና። ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቍጥር ጥቂት የነበርህ እስራኤል ሆይ፥ እኔ እረዳሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው። እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፤ ተራሮችንም ታሄዳለህ፤ ኮረብቶችንም ታደቅቃቸዋለህ እንደ ገለባም ታደርጋቸዋለህ። ታበጥራቸዋለህ፤ ነፋስም ይጠርጋቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ አንተም በእስራኤል ቅዱስ ደስ ይልሃል። ድሆችና ምስኪኖች ውኃ ይሻሉ፤ አያገኙምም፤ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፤ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በተራሮች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የተጠማችውንም ምድር ለውኃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን፥ ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር እጅ ይህን ሁሉ እንደ ሠራ፥ የእስራኤልም ቅዱስ ይህን እንደ አሳየ ያውቁ ዘንድ፥ ያስተውሉም ዘንድ፥ ይረዱም ዘንድ፥ ያምኑም ዘንድ ነው።
ትንቢተ ኢሳይያስ 41 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 41:10-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች