ትንቢተ ኢሳይያስ 41:10-20

ትንቢተ ኢሳይያስ 41:10-20 አማ54

እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፥ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። እነሆ፥ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ይዋረዱማል፥ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፥ ይጠፉማል። የሚያጣሉህንም ትሻቸዋለህ አታገኛቸውምም፥ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ። እኔ አምላክህ እግዚአብሔር፦ አትፍራ፥ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝህን እይዛለሁና። አንተ ትል ያዕቆብ የእስራኤልም ሰዎች ሆይ፥ አትፍሩ፥ እረዳሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው። እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፥ ተራሮችንም ታሄዳለህ ታደቅቃቸውማለህ፥ ኮረብቶችንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ታበጥራቸዋለህ፥ ንፋስም ይጠርጋቸዋል፥ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፥ አንተም በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በእስራኤልም ቅዱስ ትመካለህ። ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፥ እኔ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆዎችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፥ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የጥማትንም ምድር ለውሃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። የእግዚዘብሔር እጅ ይህን እንደ ሠራች፥ የእስራኤልም ቅዱስ እንደ ፈጠረው ያዩ ዘንድ ያውቁም ዘንድ ያስቡም ዘንድ በአንድነትም ያስተውሉ ዘንድ፥ በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፥ በበረሃውም ጥዱንና አስታውን ወይራውንም በአንድነት አኖራለሁ።