ትን​ቢተ ኢሳ​ይ​ያስ 41:1-10

ትን​ቢተ ኢሳ​ይ​ያስ 41:1-10 አማ2000

ደሴ​ቶች ሆይ፥ ወደ እኔ ተመ​ለሱ፤ አለ​ቆች ኀይ​ላ​ቸ​ውን ያድ​ሳ​ሉና በአ​ን​ድ​ነት ቀር​በው ፍር​ድን ይና​ገሩ። ከም​ሥ​ራቅ ጽድ​ቅን ያስ​ነሣ፥ ይከ​ተ​ለ​ውም ዘንድ ወደ እግሩ የጠ​ራው ማን ነው? በአ​ሕ​ዛ​ብና በነ​ገ​ሥ​ታት ፊት ድን​ጋ​ጤን ያመ​ጣል። ጦሮ​ቻ​ቸ​ውን በም​ድር ያስ​ጥ​ላ​ቸ​ዋል፤ ቀስ​ቶ​ቻ​ቸ​ውም እንደ ገለባ ይረ​ግ​ፋሉ። ያሳ​ድ​ዳ​ቸ​ዋ​ልም፤ እግ​ሮ​ቹም በሰ​ላም መን​ገድ ይሄ​ዳሉ። ይህን የሠ​ራና ያደ​ረገ፥ ትው​ል​ድ​ንም ከጥ​ንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊተ​ኛ​ውና ኋለ​ኛው እኔ ነኝ። አሕ​ዛብ አይ​ተው ፈሩ። የም​ድ​ርም ዳር​ቾች ቀረቡ፤ በአ​ን​ድ​ነ​ትም ቀረቡ፤ መጡም። ሁሉም ባል​ን​ጀ​ራ​ውን ይከ​ራ​ከ​ራል፤ ሁሉም እያ​ን​ዳ​ንዱ ወን​ድሙ ይረ​ዳው ነበር፤ ወን​ድ​ሙ​ንም፦ አይ​ዞህ ይለው ነበር። አና​ጢ​ውም አን​ጥ​ረ​ኛ​ውን፥ በመ​ዶ​ሻም የሚ​ያ​ሳ​ሳ​ውን መስፍ መች​ውን አጽ​ናና፤ ስለ ማጣ​በቅ ሥራ​ውም፥ “መል​ካም ነው” አለ፤ እን​ዳ​ይ​ን​ቀ​ሳ​ቀ​ስም በች​ን​ካር አጋ​ጠ​መው። ባሪ​ያዬ እስ​ራ​ኤል፥ የመ​ረ​ጥ​ሁህ ያዕ​ቆብ፥ የወ​ዳጄ የአ​ብ​ር​ሃም ዘር ሆይ፥ አንተ ከም​ድር ዳርቻ የያ​ዝ​ሁህ፥ ከማ​ዕ​ዘ​ን​ዋም የጠ​ራ​ሁህ ነህና፦ አንተ ባሪ​ያዬ ነህ፤ መር​ጬ​ሃ​ለሁ፤ አል​ጥ​ል​ህም፤ ያል​ሁህ ሆይ፥ እኔ ከአ​ንተ ጋር ነኝና አት​ፍራ፤ እኔ አም​ላ​ክህ ነኝና አት​ደ​ን​ግጥ፤ አበ​ረ​ታ​ሃ​ለሁ፤ እረ​ዳ​ህ​ማ​ለሁ፤ በጽ​ድ​ቄም ቀኝ ደግፌ እይ​ዝ​ሃ​ለሁ።