ኢሳይያስ 41:1-10
ኢሳይያስ 41:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ደሴቶች ሆይ፥ ወደ እኔ ተመለሱ፤ አለቆች ኀይላቸውን ያድሳሉና በአንድነት ቀርበው ፍርድን ይናገሩ። ከምሥራቅ ጽድቅን ያስነሣ፥ ይከተለውም ዘንድ ወደ እግሩ የጠራው ማን ነው? በአሕዛብና በነገሥታት ፊት ድንጋጤን ያመጣል። ጦሮቻቸውን በምድር ያስጥላቸዋል፤ ቀስቶቻቸውም እንደ ገለባ ይረግፋሉ። ያሳድዳቸዋልም፤ እግሮቹም በሰላም መንገድ ይሄዳሉ። ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር ፊተኛውና ኋለኛው እኔ ነኝ። አሕዛብ አይተው ፈሩ። የምድርም ዳርቾች ቀረቡ፤ በአንድነትም ቀረቡ፤ መጡም። ሁሉም ባልንጀራውን ይከራከራል፤ ሁሉም እያንዳንዱ ወንድሙ ይረዳው ነበር፤ ወንድሙንም፦ አይዞህ ይለው ነበር። አናጢውም አንጥረኛውን፥ በመዶሻም የሚያሳሳውን መስፍ መችውን አጽናና፤ ስለ ማጣበቅ ሥራውም፥ “መልካም ነው” አለ፤ እንዳይንቀሳቀስም በችንካር አጋጠመው። ባሪያዬ እስራኤል፥ የመረጥሁህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፥ አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ፥ ከማዕዘንዋም የጠራሁህ ነህና፦ አንተ ባሪያዬ ነህ፤ መርጬሃለሁ፤ አልጥልህም፤ ያልሁህ ሆይ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፤ እረዳህማለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።
ኢሳይያስ 41:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ደሴቶች ሆይ፤ በፊቴ ዝም በሉ፤ አሕዛብ ኀይላቸውን ያድሱ! ቀርበው ይናገሩ፤ በፍርድም ፊት እንገናኝ። “ከምሥራቅ አንዱን ያነሣው፣ በጽድቅም ወደ አገልግሎቱ የጠራው ማን ነው? አሕዛብን አሳልፎ ሰጠው፤ ነገሥታትን በፊቱ አስገዛለት በሰይፉም እንደ ትቢያ አቦነናቸው፤ በቀስቱም በነፋስ እንደ ተበተነ ገለባ አደረጋቸው። አሳደዳቸው፤ በሰላም ዐልፎ ሄደ፤ እግሩም ቀድሞ ባልረገጠው መንገድ ተጓዘ። ይህን የሠራና ያደረገ፣ ትውልድን ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር ከፊተኛው፣ ከኋለኛውም ጋራ፤ እኔው ነኝ።” ደሴቶች አይተው ፈሩ፤ የምድር ዳርቾች ደነገጡ፤ ቀረቡ፤ ወደ ፊትም መጡ። እያንዳንዱ ይረዳዳል፤ ወንድሙንም፣ “አይዞህ!” ይለዋል። የእጅ ጥበብ ባለሙያው የወርቅ አንጥረኛውን ያበረታታዋል፤ በመዶሻ የሚያሳሳውም፣ በመስፍ ላይ የሚቀጠቅጠውን ያነቃቃዋል፤ ስለ ብየዳም ሥራው፣ “መልካም ነው” ይለዋል፤ የጣዖቱ ምስል እንዳይወድቅም በምስማር ያጣብቀዋል። “አንተ ግን፣ ባሪያዬ እስራኤል፣ የመረጥሁህ ያዕቆብ፣ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፤ ከምድር ዳርቻ ያመጣሁህ፣ ከአጥናፍም የጠራሁህ፣ ‘አንተ ባሪያዬ ነህ’ ያልሁህ፤ መረጥሁህ እንጂ አልጣልሁህም። እኔ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።
ኢሳይያስ 41:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደሴቶች ሆይ፥ በፊቴ ዝም በሉ፥ አሕዛብም ኃይላቸውን ያድሱ፥ ይቅረቡም በዚያን ጊዜም ይናገሩ፥ ለፍርድ በአንድነት እንቅረብ። ከምሥራቅ አንዱን ያስነሣ በጽድቅም ወደ እግሩ የጠራው ማን ነው? አሕዛብንም አሳልፎ በፊቱ ሰጠው፥ ነገሥታትንም አስገዛለት፥ ለሰይፉ እንደ ትቢያ ለቀስቱም እንደ ተጠረገ እብቅ አድርጎ ሰጣቸው። አሳደዳቸው፥ እግሮቹም አስቀድመው ባልሄዱባት መንገድ በደኅንነት አለፈ። ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራው ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር፥ ፊተኛው በኋለኞችም ዘንድ የምኖር፥ እኔ ነኝ። ደሴቶች አይተው ፈሩ፥ የምድርም ዳርቾች ተንቀጠቀጡ፥ ቀረቡም ደረሱም። ሁሉም እያንዳንዱ ባልንጀራውን ይረዳው ነበር፥ ወንድሙንም፦ አይዞህ ይለው ነበር። አናጢውም አንጥረኛውን፥ በመዶሻም የሚያሳሳውን መስፍ መችውን አጽናና፥ ስለ ማጣበቅ ሥራውም፦ መልካም ነው አለ፥ እንዳይንቀሳቀስም በችንካር አጋጠመው። ባሪያዬ እስራኤል፥ የመረጥሁህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፥ አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ ከማዕዘንዋም የጠራሁህና፦ አንተ ባሪያዬ ነህ መርጬሃለሁ አልጥልህም ያልሁህ ሆይ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፥ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።
ኢሳይያስ 41:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ በደሴቶች የምትኖሩ ሕዝቦች! ጸጥ ብላችሁ አድምጡ! ሕዝቦች ኀይላቸውን ያድሱ፤ ወደ ፊትም ቀርበው ይናገሩ፤ በፍርድ ሸንጎ በአንድነት እንገናኝ። “ድል አድራጊውን አነሣሥቶ ከምሥራቅ ያመጣ፥ እንዲያገለግለው የጠራው ማነው? ሕዝቦችን አሳልፎ ለእርሱ ይሰጣቸዋል። ነገሥታትንም ያስገዛለታል፤ በሰይፉ እንደ ትቢያ በፍላጻዎቹም እንደ ገለባ ይበታትናቸዋል። ከዚህ በፊት እግሮቹ ሄደውበት በማያውቁት መንገድ እነርሱን በፍጥነት ሲያሳድድ ምንም ጒዳት አይደርስበትም። ይህ እንዲሆን የፈቀደ ማን ነው? የታሪክንስ ሂደት የሚቈጣጠር ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ ነበርኩ፤ በመጨረሻም የምገኝ እኔው ነኝ። “በደሴቶች የሚኖሩ ሕዝቦች እኔ ያደረግኹትን ሁሉ አይተዋል፤ ስለዚህም እጅግ ደንግጠው ተንቀጥቅጠዋል፤ በአንድነትም ተሰብስበው ወደ እኔ መጥተዋል። አንዱ ሌላውን ይረዳል፤ ወንድምም ወንድሙን ‘አይዞህ በርታ፤’ ይለዋል። የእጅ ጥበብ ዐዋቂው ወርቅ አንጥረኛን ያበረታታዋል፤ ጣዖት ጠርቦ በመዶሻ የሚያለሰልሰውም በመስፍ ላይ የሚመታውን ‘አይዞህ በርታ! ብየዳው መልካም ነው!’ ይለዋል። እንዳይንቀሳቀስም ጣዖቱን በምስማር ይቸነክሩታል።” “ነገር ግን አንተ አገልጋዬ እስራኤል ሆይ! ሕዝቤ እንድትሆን የመረጥኩህ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ነህ። ከምድር ዳርቻ አመጣሁህ፥ ከአራቱም ማእዘን ጠራሁህ፤ ‘አገልጋዬ ትሆናለህ’ ብዬ መረጥኩህ እንጂ አልጣልኩህም። እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ! እኔ አምላክህ ነኝ፥ ተስፋ አትቊረጥ! እኔ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፤ ድል ነሺ በሆነ ክንዴ እደግፍሃለሁ።
ኢሳይያስ 41:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ደሴቶች ሆይ፥ በፊቴ ዝም በሉ፤ አሕዛብም ኃይላቸውን ያድሱ፤ ይቅረቡም በዚያን ጊዜም ይናገሩ፤ ለፍርድ በአንድነት እንቅረብ። ከምሥራቅ አንዱን ያስነሣ፥ በጽድቅም ወደ እግሩ የጠራው ማን ነው? አሕዛብንም አሳልፎ በፊቱ ሰጠው፥ ነገሥታትንም አስገዛለት፤ ለሰይፉ እንደ ትቢያ ለቀስቱም እንደ ተጠረገ እብቅ አድርጎ ሰጣቸው። አሳደዳቸው፥ እግሮቹም አስቀድመው ባልሄዱባት ሰላማዊ መንገድ አለፈ። ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራው ማን ነው? እኔ ጌታ፥ መጀመሪያም እስከ መጨረሻውም የምኖር፥ እኔ ነኝ። ደሴቶች አይተው ፈሩ፥ የምድርም ዳርቾች ተንቀጠቀጡ፤ ቀረቡም ደረሱም። ሁሉም እያንዳንዱ ባልንጀራውን ይረዳው ነበር፥ ወንድሙንም፦ “አይዞህ” ይለው ነበር። አናጢውም አንጥረኛውን፥ በመዶሻም የሚያሳሳውን በመስፍ ላይ የሚቀጠቅጠውን ያጽናናዋል፥ ስለ ብየዳ ሥራውም፦ “መልካም ነው” ይለዋል፤ እንዳይላቀቅም በችንካር ያጋጥመዋል። አገልጋዬ እስራኤል፥ የመረጥኩህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፥ አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ ከማዕዘንዋም የጠራሁህና፦ “አንተ አገልጋዬ ነህ፥ መርጬሃለሁ፥ አልጥልህም!” ያልሁህ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳሀለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።