ትንቢተ ኢሳይያስ 41:1-10

ትንቢተ ኢሳይያስ 41:1-10 አማ05

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ በደሴቶች የምትኖሩ ሕዝቦች! ጸጥ ብላችሁ አድምጡ! ሕዝቦች ኀይላቸውን ያድሱ፤ ወደ ፊትም ቀርበው ይናገሩ፤ በፍርድ ሸንጎ በአንድነት እንገናኝ። “ድል አድራጊውን አነሣሥቶ ከምሥራቅ ያመጣ፥ እንዲያገለግለው የጠራው ማነው? ሕዝቦችን አሳልፎ ለእርሱ ይሰጣቸዋል። ነገሥታትንም ያስገዛለታል፤ በሰይፉ እንደ ትቢያ በፍላጻዎቹም እንደ ገለባ ይበታትናቸዋል። ከዚህ በፊት እግሮቹ ሄደውበት በማያውቁት መንገድ እነርሱን በፍጥነት ሲያሳድድ ምንም ጒዳት አይደርስበትም። ይህ እንዲሆን የፈቀደ ማን ነው? የታሪክንስ ሂደት የሚቈጣጠር ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ ነበርኩ፤ በመጨረሻም የምገኝ እኔው ነኝ። “በደሴቶች የሚኖሩ ሕዝቦች እኔ ያደረግኹትን ሁሉ አይተዋል፤ ስለዚህም እጅግ ደንግጠው ተንቀጥቅጠዋል፤ በአንድነትም ተሰብስበው ወደ እኔ መጥተዋል። አንዱ ሌላውን ይረዳል፤ ወንድምም ወንድሙን ‘አይዞህ በርታ፤’ ይለዋል። የእጅ ጥበብ ዐዋቂው ወርቅ አንጥረኛን ያበረታታዋል፤ ጣዖት ጠርቦ በመዶሻ የሚያለሰልሰውም በመስፍ ላይ የሚመታውን ‘አይዞህ በርታ! ብየዳው መልካም ነው!’ ይለዋል። እንዳይንቀሳቀስም ጣዖቱን በምስማር ይቸነክሩታል።” “ነገር ግን አንተ አገልጋዬ እስራኤል ሆይ! ሕዝቤ እንድትሆን የመረጥኩህ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ነህ። ከምድር ዳርቻ አመጣሁህ፥ ከአራቱም ማእዘን ጠራሁህ፤ ‘አገልጋዬ ትሆናለህ’ ብዬ መረጥኩህ እንጂ አልጣልኩህም። እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ! እኔ አምላክህ ነኝ፥ ተስፋ አትቊረጥ! እኔ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፤ ድል ነሺ በሆነ ክንዴ እደግፍሃለሁ።