መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 9
9
የንግሥተ ሳባ ጕዞ ወደ ኢየሩሳሌም
(1ነገ. 10፥1-13)
1የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በግመሎች ላይ ሽቱና ብዙ ወርቅ፥ የከበረም ዕንቍ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የከበረ ድንጋይ” ይላል። አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ሰሎሞንን በኢየሩሳሌም በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች፤ ወደ ሰሎሞንም በገባች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። 2ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሰሎሞንም ያልፈታው ነገር አልነበረም። 3የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፤ 4የማዕዱንም መብል፥ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፥ የሎሌዎቹንም ሥርዐት፥ አለባበሳቸውንም፥ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፥ አለባበሳቸውንም፥ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ተደነቀች። 5ንጉሡንም አለችው፥ “ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በሀገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። 6እኔ ግን መጥቼ በዐይኔ እስካየሁ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም፤ እነሆ፥ የጥበብህን ታላቅነት እኩሌታ አልነገሩኝም፤ በሀገሬ ከሰማሁትም ዝና ይልቅ ጨመርህልኝ። 7እነዚህ ሰዎችህ ምስጉኖች ናቸው፤ በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙና ጥበብህን የሚሰሙ እነዚህ አገልጋዮችህም ምስጉኖች ናቸው። 8በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ንጉሥ እንድትሆን በዙፋኑ ላይ ያስቀምጥህ ዘንድ የወደደህ አምላክህ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን፤ አምላክህ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘለዓለም ያጸናቸው ዘንድ ወድዶአቸዋልና ስለዚህ ፍርድንና ጽድቅን ታደርግ ዘንድ በላያቸው አነገሠህ።”
9ለንጉሡም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፥ እጅግም ብዙ ሽቱ፥ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባም ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ ሽቱ ከቶ አልነበረም። 10የኪራም አገልጋዮችና የሰሎሞን አገልጋዮችም ከሴፌር ለሰሎሞን ወርቅ አመጡ፤ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቍም ደግሞ አመጡ። 11ንጉሡም ከሰንደሉ እንጨት ለእግዚአብሔር ቤትና ለንጉሡ ቤት ደርብ፥ ለመዘምራኑም መሰንቆና በገና አደረገ፤ እንደዚህም ያለ በይሁዳ ምድር ከቶ አልታየም ነበር። 12እርስዋም ለንጉሡ ለሰሎሞን ካመጣችው የበለጠ፥ ንጉሡ ሰሎሞን የወደደችውን ሁሉ፥ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፤ እርስዋም ተመልሳ ከአገልጋዮችዋ ጋር ወደ ሀገርዋ ሄደች።
የንጉሥ ሰሎሞን ሀብት ብዛት
(1ነገ. 10፥14-25)
13በየዓመቱም ወደ ሰሎሞን የሚመጣ የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ። 14ነጋድራሶችና ነጋዴዎች ከሚያመጡት ሌላ የዓረብ ነገሥታት ሁሉ፥ የምድሩም ሹሞች ወደ ንጉሡ ሰሎሞን ወርቅና ብር ያመጡ ነበር 15ንጉሡም ሰሎሞን በጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላባሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በየአንዳንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው የጠራ ወርቅ ስድስት መቶ ሰቅል ነበረ። 16ከጥፍጥፍም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በየአንዳንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበረ፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው። 17ንጉሡም ደግሞ ከዝሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። 18ወደ ዙፋኑም የሚያስሄዱ፥ በወርቅ የተለበጡ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ በዚህና በዚያ በመቀመጫው አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፤ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር። 19በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። 20ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ የወርቅ ነበረ፤ የሊባኖስ ዱር በተባለውም ቤቱ የሚገለገልበት ዕቃ ሁሉ ጥሩ ወርቅ ነበረ፤ በሰሎሞንም ዘመን ብር ከቶ አይቈጠርም ነበር። 21ለንጉሡም ከኪራም አገልጋዮች ጋር ወደ ተርሴስ የሚሄዱ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር፥ የዝሆንም ጥርስና ዝንጀሮ#ዕብ. “ዝንጉርጉር ወፍም” የሚል ይጨምራል። ይዘው ይመጡ ነበር።
22ንጉሡም ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ በባለጠግነትና በጥበብ በለጠ። 23የምድርም ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበቡን ይሰሙ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ሊያዩ ይመኙ ነበር። 24ከእነርሱም እያንዳንዱ ገጸ በረከቱን፥ የወርቅንና የብርን ዕቃ፥ ልብስንና የጦር መሣሪያን፥ ሽቱውንም፥ ፈረሶችንና በቅሎዎችን እየያዘ በየዓመቱ ያመጣ ነበር። 25ሰሎሞንም ለሰረገሎች አራት ሺህ እንስት ፈረሶችና#ዕብ. “ለፈረሶችና ለሰረገሎች አራት ሺህ ጋጥ” ይላል። ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎችም ከተሞች፥ ከንጉሡ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። 26ከኤፍራጥስም#“ከኤፍራጥስም” የሚለው በዕብ. ብቻ። ወንዝ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብፅ ዳርቻ ድረስ ባሉ ነገሥታት ሁሉ ላይ ነገሠ። 27ንጉሡም ወርቁንና ብሩን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ፥ የዝግባውንም እንጨት በቆላ እንደሚበቅል ሾላ ብዛት አደረገው። 28ለሰሎሞንም ፈረሶች ከግብፅና ከየሀገሩ ሁሉ ይመጡለት ነበር።
29የቀረውም ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በአኪያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በኢዩሔል#ዕብ. “አዶ” ይላል። ራእይ የተጻፈ አይደለምን? 30ሰሎሞንም በኢየሩሳሌም በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ። 31ሰሎሞንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም ሮብዓም በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 9: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ