መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 8
8
1እንዲህም ሆነ፤ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት የሠራበት ሃያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ 2ኪራም ለሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ሰሎሞን ሠራቸው፤ የእስራኤልንም ልጆች አኖረባቸው።
3ሰሎሞንም ወደ ኤማትሱባ ሄደ፤ በረታባትም። 4በምድረ በዳም ያለውን ተድሞርን፥ በኤማትም የጸኑ ከተሞችን ሁሉ ሠራ። 5ደግሞም ቅጥርና መዝጊያ፥ መወርወሪያም የነበራቸውን የተመሸጉትን ከተሞች ላይኛውን ቤትሖርን፥ ታችኛውንም ቤትሖርን ሠራ። 6ባዕላትንም፥ ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፥ የሰረገላውንም ከተሞች ሁሉ፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም፥ በሊባኖስም፥ በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ።
7ከኬጤዎናውያን፥ ከአሞሬዎናውያን፥ ከፌርዜዎናውያንም፥ ከኤዎናውያንም፥ ከኢያቡሴዎናውያንም የቀሩትን፥ ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ፥ 8የእስራኤልም ልጆች ያላጠፉአቸውን፥ በኋላቸውም በምድር ላይ የቀሩትን ልጆቻቸውን ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አደረጋቸው። 9ሰሎሞንም በመንግሥቱ ከእስራኤል ልጆች ማንንም አገልጋይ አላደረገም፤ እነርሱ ሰልፈኞች፥ የሹሞችም አለቆች፥ የሰረገሎችና የፈረሰኞች ባልደራሶች ነበሩና። 10እነዚህም በሕዝቡ ላይ ያለውን ሥራ የሚቈጣጠሩ የንጉሡ የሰሎሞን ዓይነተኞች አለቆች ሁለት መቶ አምሳ ነበሩ።
11ሰሎሞንም፥ “የእግዚአብሔር ታቦት የገባችበት ስፍራ ቅዱስ ነውና ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤት አትቀመጥም” ሲል የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ ወደ ሠራላት ቤት አወጣት።
12በዚያ ጊዜም ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ፊት በሠራው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። 13ሙሴም እንዳዘዘ እንደ ሥርዐታቸው በየቀኑ ሁሉ፥ በየሰንበታቱም፥ በየመባቻዎቹም፥ በየበዓላቱም፥ በየዓመቱ ሦስት ጊዜ በየቂጣው በዓልና በየሰባቱ ሱባዔ በዓል፥ በየዳሱም በዓል ቍርባን ያቀርቡ ነበር።
14የእግዚአብሔርም ሰው ዳዊት እንዲህ አዝዞ ነበርና ካህናቱን እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሥርዐት በየአገልግሎታቸው ሰሞን ከፈላቸው፤ ሌዋውያንም እንደ ሥርዐታቸው ያመሰግኑ ዘንድ፥ በካህናቱም ፊት ያገለግሉ ዘንድ በየሰሞናቸው ከፈላቸው፤ በረኞቹንም ደግሞ በየበሩ ሁሉ በየሰሞናቸው ከፈላቸው። 15እነርሱም ንጉሡ ስለ ነገሩ ሁሉና ስለ መዝገቡ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ያዘዘውን ነገር ሁሉ አልተላለፉም። 16እነሆ፥ መሠረቱ ከተጣለ ጀምሮ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤት እስከ ፈጸመ ድረስ ሥራው ሁሉ የተዘጋጀ ነበረ። የእግዚአብሔርም ቤት ተፈጸመ።
17ሰሎሞንም የዚያን ጊዜ በኤዶምያስ ምድር በባሕር ዳር ወዳሉ ወደ ጋሴዎንጋብርና ወደ ኤላት ሄደ። 18ኪራምም መርከቦችንና የባሕርን ነገር የሚያውቁትን መርከበኞች በአገልጋዮቹ እጅ ላከለት፤ እነርሱም ከሰሎሞን አገልጋዮች ጋር ወደ ሴፌር መጡ፤ ከዚያም አራት መቶ አምሳ መክሊት ወርቅ ወስደው ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን አመጡ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 8: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ