መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 3
3
ሰሎሞን ቤተ መቅደስ እንደ ሠራ
(1ነገ. 6፥1-38)
1ሰሎሞንም እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በአሞሪያ ተራራ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ። 2በነገሠም በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር መሥራት ጀመረ። 3ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት ይሠራ ዘንድ የጣለው መሠረት ይህ ነው፤ ርዝመቱም በዱሮው ስፍር ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበረ። 4በቤቱም ፊት የነበረው ወለል ርዝመቱ እንደ ቤቱ ወርድ ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም መቶ ሃያ ክንድ ነበረ፤ ውስጡንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው። 5ታላቁንም ቤት በዝግባ እንጨት ከደነው፤ በጥሩም ወርቅ ለበጠው፤ የዘንባባና የሰንሰለት አምሳልም ቀረጸበት። 6ቤቱንም በከበረና በተመረጠ ዕንቍ፥ በወርቅም አስጌጠው፤ ወርቁም የፋሩሔም ወርቅ ነበረ። 7ቤቱንም፥ ሰረገሎቹንም፥ መድረኮቹንም፥ ግንቦቹንም፥ ደጆቹንም በወርቅ ለበጠ፤ በግንቦቹም ላይ ኪሩቤልን ቀረጸ።
8ቅድስተ ቅዱሳኑንም ሠራ፤ ርዝመቱም እንደ ቤቱ ወርድ ሃያ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበረ፤ ስድስት መቶ መክሊት በሚያህል በጥሩ ወርቅም ኪሩቤልን#“ኪሩቤልን” የሚለው በዕብ. የለም። ለበጣቸው። 9የምስማሮቹም ሚዛን ለእያንዳንዱ አምሳ ሰቅል ወርቅ ነበረ። የደርቡንም ጓዳዎች በወርቅ ለበጠ።
10በቅድስተ ቅዱሳንም ውስጥ ከእንጨት ሥራ ሁለቱን ኪሩቤል ሠራ፤ በወርቅም ለበጣቸው። 11የኪሩቤልም ክንፎች ሃያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱ የኪሩብ ክንፍ ርዝመት አምስት ክንድ ነበረ፤ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለተኛውም ክንፍ ርዝመት አምስት ክንድ ነበረ፤ የሁለተኛውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 12የሁለተኛውም ኪሩብ አንዱ ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ የቤቱንም ግንብ ይነካ ነበር፤ ሁለተኛውም ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ የሌላውንም ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 13የእነዚህም ኪሩቤል ክንፎች ሃያ ክንድ ሙሉ ተዘርግተው ነበር፤ በእግራቸውም ቆመው ነበር፤ ፊቶቻቸውም ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመለከቱ ነበር።
14ከሰማያዊውም፥ ከሐምራዊውም፥ ከቀዩም ሐር፥ ከጥሩም በፍታ መጋረጃውን ሠራ፤ ኪሩቤልንም ጠለፈበት።
15በቤቱም ፊት ቁመታቸው ሠላሳ አምስት ክንድ የነበረውን ሁለቱን ዐምዶች ሠራ፤ በእያንዳንዳቸውም ላይ የነበረው ጕልላት አምስት ክንድ ነበረ።
16እንደ ድሪ ያሉ ሰንሰለቶችንም ሠርቶ በአዕማዱ ራስ ላይ አደረጋቸው፤ መቶም ሮማኖች ሠርቶ በሰንሰለቱ ላይ አደረጋቸው። 17አዕማዶቹንም አንደኛውን በቀኝ፥ ሁለተኛውንም በግራ በመቅደሱ ፊት አቆማቸው፤ በቀኝም የነበረውን ስም ርትዕ#ዕብ. “ያቁም” ይላል። በግራም የነበረውን ስም ጽንዕ#ዕብ. “በለዝ” ይላል። ብሎ ጠራቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 3: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ