መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 4
4
ለቤተ እግዚአብሔር የሚያገለግሉ ንዋያተ ቅድሳት
(1ነገ. 7፥23-51)
1ርዝመቱም ሃያ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም ዐሥር ክንድ#በግእዝ “ሃያ ክንድ” ይላል። የነበረውን የናሱን መሠዊያ ሠራ። 2ዳግመኛም ከቀለጠ ናስ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፥ ቁመትዋም አምስት ክንድ፥ ዙሪያዋም ሠላሳ ክንድ የሆነ ኵሬ ሠራ። 3በበታችዋም፥ በዙሪያዋ በዐሥሩ ክንድ የበሬዎች ምስሎች ነበሩ። ኵሬዋንም ይከብቡአት ነበር። በሬዎቹም በሁለት ተራ ሁነው ከኵሬው ጋር በአንድነት ቀልጠው የተሠሩ ነበሩ። 4ዐሥራ ሁለት በሬዎችን ሠሩላቸው። ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱ ወደ ምዕራብ፥ ሦስቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር፤ ቀልጣ የተሠራች ኵሬም በላያቸው ነበረች፤ የሁሉም ጀርባቸው በስተውስጥ ነበረ። 5ውፍረትዋም አንድ ጋት ያህል ነበረ፤ ከንፈሯም እንደ ጽዋ ከንፈር፥ እንደ ሱፍ አበባ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ሦስት ሺህም ማድጋ ትይዝ ነበር ሠርቶም ፈጸማት፤ 6ደግሞም ዐሥር የመታጠቢያ ሰኖችን ሠራ፤ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበው ነገር ሁሉ ይታጠብባቸው ዘንድ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ አኖራቸው፤ ባሕሩ ግን ካህናት ይታጠቡበት ነበር።
7ዐሥሩንም የወርቅ መቅረዞች እንደ ሥርዐታቸው ሠራ፤ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። 8ዐሥሩንም የወርቅ ገበታዎች ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። አንድ መቶም የወርቅ ጽዋዎችን ሠራ። 9ደግሞም የካህናቱን አደባባይ ፥ ታላቁንም አደባባይ፥ የአደባባዩንም ደጆች ሠራ፤ ደጆቻቸውንም በናስ ለበጠ። 10ኵሬውንም በቤተ መቅደሱ መዓዝን በስተቀኝ በኩል በምሥራቅ አቅጣጫ አኖረው።
11ኪራምም ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹን፥ በመሠዊያው ቤት ያሉ#“በመሠዊያው ቤት” በዕብ. የለም። ማንኪያዎችንና የመገልገያውን ዕቃ ሁሉ ሠራ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ። 12ሁለት ዐምዶችንና በሁለቱ ዐምዶች ላይ ጕልላቶችን፥ በዐምዶቹም ራሶች ላይ ያሉትን ጕልላቶች የሚሸፍኑ ሁለት መርበቦችን ሠራ። 13በሁለቱም መርበቦች አራት መቶ የወርቅ ሻኵራዎችንና በዐምዶቹ ላይ ያሉትን ሁለት ጕልላቶች በሁለት ጎኖች የሚሸፍኑትን ሮማኖች ሠራ። 14ዐሥር መቀመጫዎችንና በመቀመጫዎቹም ላይ መታጠቢያዎችን ሠራ፤ 15አንድዋንም ኵሬ፥ በበታችዋም ያሉትን ዐሥራ ሁለት በሬዎች ሠራ። 16የእግር መታጠቢያዎችን፥ የእጅ መታጠቢያዎችን፥ ጋኖችን፥ የሥጋ ማውጫ ሜንጦዎችንና ኪራም የሠራውን ሥራ ሁሉ ከንጹሕ ናስ ሠርቶ ለንጉሡ ለሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤት አቀረበለት። 17ንጉሡም በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በሴድራ መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አቀለጣቸው። 18ሰሎሞንም እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ እጅግ አብዝቶ ሠራ፤ የናሱም ብዛት አይቈጠርም ነበር።
19ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ፥ የወርቁንም መሠዊያ፥ ኅብስተ ገጽ የነበረባቸውን ገበታዎች ሠራ። 20በመቅደሱ ፊት እንደ ሥርዐታቸው የሚያበሩ መቅረዞችንና ቀንዲሎችንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። 21የመብራቶች መቅረዞችንና በላያቸው ያሉ መብራቶችን፥ ጽዋዎቹን፥ ማንኪያዎቹን፥ ሥራ የሚሠሩባቸው ጻሕሎችንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። 22ውስጠኛው የእግዚአብሔር ቤት ደጅና ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ የሚወስደው የውስጠኛውም የቤተ መቅደሱ ደጆች የወርቅ ነበሩ። እንዲሁም ሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት የሠራው ሥራ ሁሉ ተፈጸመ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 4: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ