መጽሐፈ ጥበብ 8

8
1ከዓለም አንድ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ በኃይል ትዘረጋለች፤
መላውንም ዓለም ስለደኀንነቱ ስትል ታስተዳድራለች።
ሰሎሞን ለጥበብ ያለው ፍቅር
2ከወጣትነቴ ጀምሮ ጥበብን አፈቀርሁ፥
ፈለግኋትም፤ ሙሽራዬም ላደርጋት ወሰንሁ፤ በውበቷ ተረታሁ።
3የእግዚአብሔርን ሕይወት በመጋራት የተከበረ የትውልድ ሐረጓን ይበልጥ ከፍ ከፍ አአደረገች፤
የሁሉም ጌታ የሆነው አምላክም ይወዳታል።
4በእርግጥ የእግዚአብሔርን እውቀት፥ ምስጢራትም ትጋራለች፤
የሚሠራውንም የምትመርጥ እርሷ ነች።
5በዚህኛው ሕይወት ሃብትን ማግኘት ካስፈለገ፥
የሁሉም ነገር ፈጣሪ ከሆነችው ጥበብ የበለጠ ሃብታም ከወዴት ይገኛል
6የሚፈለገው በሥራ ላይ ያለው ዕውቀትም ከሆነ፥
ፍጡራኑን ሁሉ ከነደፈች ከጥበብ የተሻለ ይኖራልን
7የምታፈቅረው ጽድቅን ከሆነ
መልካም ምግባር የሥራዋ ፍሬ ነው፤
ቁጥብነትንና ጥንቁቅነትን፥
ፍትሕንና ጽናትንም የምታስተምር እርሷ ነችና።
8ሰፊ ተሞክሮ ለማግኘት የጓጓም ካለ፥
ያለፈውን ታውቃለች፥ መጪውንም ትተነቢያለች፤
ምሳሌዎችን የምትተረጉም፥ እንቆቅልሾችን የምትፈታ ነች፤
ምልክቱንና ድንቅ ነገሮችን፥
የዓመታትና የዘመናትንም አመጣጥ ታውቃለች።
9እኔ ሕይወቴን ትጋራ ዘንድ፥
ጥበብን ተቀበልኋት፤ በብልጽግና ጊዜ አማካሪዬ፥
በችግርና በመከራ ደግሞ አጽግኚዬ እንደምትሆን አውቃለሁና።
10በእርሷ ምክንያት ብዙሃኑ ያደንቁኛል፤
ወጣት ብሆንም እንኳ በሽማግሌዎች ዘንድ የተከበርሁ ነኝ።
11በምሰጠው ዳኝነት ብልኀነቴ ይታያል፤
ታላላቆችም በእኔ ይደነቃሉ፤
12በዝምታዎቼ ወቅት ይጠባበቃሉ፤
ስናገር በጥሞና ያዳምጣሉ፤ ረዘም ላለ ጊዜ ከተናገርሁ፥
እጆቻቸውን በከንፈሮቻቸው ላይ የደርጋሉ።
13በእርሷ አማካኝነት ሕያውነትን አገኛለሁ፤
ለተተኪዎቼም ዘላለማዊ መታሰቢያን እተዋለሁ።
14ሕዝቦችን እገዛለሁ፤ ሀገሮችም ለእኔ ይገብራሉ፤
15ስሜን በሰሙ ጊዜ ጨካኝ አምባገነኖች ይንቀጠቀጣሉ፤
ጀግንነቴንና ደግነቴን ለሕዝቡ አሳያለሁ።
16ወደ ቤቴ ስመለስ የምዝናናው ከእርሷ ጋር ነው፤
እርሷ ባለችበት ምሬት የለምና።
ሕየወትን ከእርሷ ጋር ሲመሩ ሥቃይ የለም፥
ተድላና ደስታ ብቻ እንጂ።
ሰሎሞን ጥበብን ለማግኘት ተዘጋጀ
17ይህን ሁሉ አሰላስልሁ፤
ሕያውነት ከጥበብ ጋር በዝምድና መኖሯን፤
18የከበረ ደስታ ወዳጇ፥
የማያልቅ ሃብት የሥራዋ ፍሬ መሆኑን አወቅሁ፤
ተከታዮቼን በማስተማር ማስተዋልን፥
እርሷን በማነጋገር ዝናን ማትረፍ እንደሚቻል ተገነዘብሁ፤
እናም እርሷን ፈልጌ ለማግኘት ያልረገጥሁት መንገድ የለም።
19ደስታ ያልተለየኝ ልጅ ነበርሁ፤
ዕጣዬ ሆኖ የደረሰኝም ነፍስ ደግ ነች።
20እንዲያውም ጥሩ በመሆኔ፥ መኖሪያዬ እንዲሆን የተሰጠኝ ሥጋ ንጹሕ ነው።
21ነገር ግን ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ጥበብን ማግኘት እንደማይቻል በመረዳቴ፥
ጥበብ የማን ስጣታ እንደ ሆነች መረዳቱ ራሱ የማስተዋል ምልክት ነው።
ወደ ጌታ ጸለይሁ፥ ተማፀንሁት፥ ከልቤም እንዲህ አልሁ፦

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ