መጽሐፈ ጥበብ 7

7
እንደ ሌሎች ሁሉ ሰው የሆነው ሰሎሞን
1እኔም እንደሌላው ሰው ሁሉ ሟች ነኝ፤
ከመሬት የተፈጠረው የመጀመሪያ ሰው ዘር ነኝ፤
በአንዲት እናት ማሕፀን ውስጥ ከሥጋ የተሠራሁ ነኝ፤
2ለዓሥር ወራት ያህል ምግቤን ከደም አገኝ ነበር፤
ከወንድ ዘርና ከመኝታ ጓደኛው ካገኘው ደስታ የተገኘሁ ፍሬ ነኝ።
3እንደተወለድሁ እኔም አየር ስቤያለሁ፥
ሁላችንን በተሸከመችውም ምድር ላይ ወድቄያለሁ፤
እንደ ሌሎች ሁሉ የመጀመሪያው ድምፄም ለቅሶ ነበር።
4ከብዙ ጥንቃቄ ጋር በጨርቅ ተጠቅልዬ አደግሁ፤
5የትኛውም ንጉሥ ቢሆን ከዚህ የተለየ ጅማሬ የለውም።
6ምክንያቱም ሕይወት መግቢያዋ አንድ፥ መውጫዋም አንድ ነውና።
ሰሎሞን ለጥበብ የነበረው አክብሮት
7ስለዚህ ጸለይሁ፤ ማስተዋልም ተሰጠኝ፤ ልመናዬን አቀረብሁ፥
የጥበብ መንፈስም ወደ እኔ መጣ።
8ከበትረ መንግሥትና ከዙፋኑም ይልቅ፥ እርሷን ከፍ አደረግሁ፤
ከጥበብ ጋር ሲነጻጸር ሀብት ምኔም አይደለም።
9እጅግ የከበረ ድንጋይ፥ ከእርሷ አይስተካከልም፤
ወርቅም ቢሆን በእርሷ ዐይን፥ የተቆነጠረ አሸዋ አያህልም፤
ያ ከእርሷ ጋር ሲተያይ ብር፥ የጭቃ ያህል ነው።
10ከጤናና ከውበት የበለጠ አፈቅራታለሁ፤
ከብርሃን እርሷን መረጥሁ፤
ጮራዋ ምንጊዜም አይደበዝዝምና።
11መልካም መልካሙ ሁ፥ ከእርሷ ጋር ወደ እኔ ቀረበ፤
ከእጆችዋም ተቆጥሮ የማይዘለቅ ሃብት አገኘሁ።
12በጥበብ ያገኘኋቸው በመሆኑም እደሰትባቸዋለሁ፤
በመጀመሪያ ላይ ግን የሁሉም እናት እርሷ መሆኗን አላወቅሁም ነበር።
13በጥልቀት ያጠናሁትን በሰፊው አስተምራለሁ፤
የብልጽግናዋንም መጠን አልደብቅም።
14ጥበብ የው ልጅ ሲዝቃት የማታልቅ ሃብት ነች፤
ይህንን የሚያገኙ የእግዚአብሔርንም ወዳጅነት ያገኛሉ፤
የትምህርት ጸጋ ለእነርሱ ሰጥታቸዋለችና።
መለኮታዊ አነሳሽነትን ለማግኘት ሰሎሞን ያቀረበው ልመና፥
15የእነርሱን ፈቃድ እናገር ዘንድ ያብቃኝ፤
በተሰጠኝ ጸጋ መጠን መልካም ሐሳቦትን ላፍልቅ፤
እርሱ ወደ ጥበብ የሚመራ፥ ጥበበኞትንም የሚያሠማራ ነውና።
16እኛ በእርሱ እጅ ነን፤ በእርግጥም እኛም አባባሎቻችንም፥
ረቂቁም ይሁን ተግባራዊው ዕውቀት ጭምር ሁሉም የእርሱ ነው።
17ተፈጥሮን እረዳ ዘንድ፥ አስተማማኝ እውቀትን የጠኝ እርሱ ነው፤
የምድርን አቀማመጥ፥ የንጥረ ነገሮችን ጥቅም፥
18የጊዜን መጀመሪያ፥ ማብቂያውንና አጋማሹን፥ የቀናት እርዝማኔ፥ ልውውጥና የወቅቶችን መፈራረቅ፥
19የዓመትን ዑደትና የከዋክብት አቀማመጥ፥
20የእንስሳትን ተፈጥሮና የአራዊትን ደመ ነፍስ፥
የመንፈሶችን ኃይልና የሰዎችን አእምሮአዊ አሠራር፥
የተክል ዓይነቶችንና የሥሮችን ፈዋሽ ባሕርይ፥ የገለጸልኝ እርሱ ነው።
21ድብቁን ሆነ የሚታየው፤ ሁሉንም አሁን አውቄዋለሁ፤
የሁሉም ነገር ፈጣሪ የሆነች ጥበብ አስተምራኛለችና።
የጥበብ ውዳሴ
22ጥበብ አዋቂ፥ ቅዱስ፥
የተለየ ባለ ብዙ ባሕርይ ረቂቅ፥
ተንቀሳቃሽ፥ አስተዋይ፥ እንከን የለሽ፥
ግልጽ፥ የማትደፈር፥ ቅን፥ ብልኀ፥
23ኃያል፥ ደግ፥ የሰው ልጆች ወዳጅ፥
ቆራጥ፥ አስተማማኝ፥ የማትሸበር፥
ሁሉን የምትችል፥ ሁሉን የምትቆጣጠር፥
አስተዋይ፥ ንጹሕ፥ ረቂቅ፥ የሆኑትን መንፈሶች ዘልቆ የሚገባ መንፈሳዊ አካል አላት።
24ጥበብ ከማንኛውም እንቅስቃሴ ፈጥና መንቀሳቀስ ትችላለች፤
ንጹሕ በመሆኗም ሁሉንም ነገር ዘልቃ ትናኛለች።
25እርሷ የእግዚአብሔር ኃይል እስትንፋስ ነች፤
የኃያሉ አምላክ ክብርም መግለጫ ነች፤
ስለዚህም ያልነጻ ነገር በውስጧ ሊገባ አይችልም።
26የዘላለማዊ ብርሃን ነጸብራቅ፤
የእግዚአብሔር ሥራ መስተዋት፤
የደግነቱም ምስል ናትና።
27ምንም እንኳ ብቸኛ ብትሆንም፥ ሁሉንም ማድረግ የምትችል ናት፤
ራሷ ሳትለወጥ ዓለምን ታድሳለች፤
ከትውልድ ወደ ትውልድም በተቀደሱ ነፍሶች ውስጥ በማለፍ
የእግዚአብሔር ወዳጆች ነቢያትም ታደርጋቸዋለች።
28እግዚአብሔር የሚወደው ከጥበብ ጋር የሚኖሩትን ሰዎች ብቻ ነውና።
29ጥበብ ከፀሐይ ትደምቃለች፥
ከከዋክብት የበለጠ ታበራለች፥
ከብርሃን ጋር ስትነጻጸር፥ እርሷ ትበልጣለች።
30ቀን በሌት ይተካል፤ ክፋት ግን ጥበብን አይረታምና።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ