መጽሐፈ ጥበብ 6
6
የሰሎሞን የጥበብ ጥም
ነገሥታት ጥበብን ይቅሰሙ
1ነገሥታት ሆይ እንዲገባችሁ አድምጡ፤
እናንተ ሥልጣናችሁ እስከ ምድር ዳርቻ የሚደርስ ተመከሩ፤
2ታላላቅ ሕዝቦችን የምትመሩ፥
ባስገበራችኋቸው ሀገሮች ብዛት የምትታበዩ፥ እናንተ ሁላችሁ ስሙ
3ነጻነትን የሰጣችሁ ጌታ፥ ኃይልንም ሰጥቷችኋልና፤
እርሱ ራሱ ድረጊቶቻችሁን ይመረምራል፤ ዕቅዶቻችሁንም ይከታተላል።
4የመንግሥቱ አገልጋዮች እንደ መሆናችሁ፥
በትክክል ካላስተዳደራችሁ፥ ሕጉን ካላከበራችሁ፥
የእግዚአብሔርንም ፈቃድ ካልፈጸማችሁ፥
5በአስፈሪ ሁኔታ ፈጥኖ ይነሣባችኋል፤
በባለሥልጣናቱም ላይ ብርቱ ፍርድ ይሰጣል።
6የበታች ሹሞች ይታዘንላቸዋል፤ ይቅርታም ይደረግላቸዋል፤
ኃያላኑ ግን ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ።
7የሁሉም ጌታ ማንንም አይፈራምና፥
ታላቅነት እርሱን አያስደነግጠውም፤
ትንሹንና ትልቁን የፈጠረ፥
ለሁሉም የሚፈልገውን የሚሰጥ እርሱ ነውና።
8በሥልጣናቸው የሚጠቀሙ ግን ታላቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል፥
9እናንተ ነገሥታታ፥ ንግግሬ ሁሉ ለእናንተ ነው፤
ጥበብን ተማሩ፥ ራሳችሁንም ከውድቀት አድኑ።
10የተቀደሱትን ሕጐች በቅድስና የሚጠብቁ፥ ቅዱሳን ይባላሉ፤
ከእነርሱ መማር በውስጣቸው ያለውን መከላከያም ማወቅ ነው።
11ስለዚህ የምናገረውን ልብ በሉ፤ በተመስጦ አድምጡ፤
ትምህርት ታገኛላችሁ፤ ጥበብንም የፈለገ ያገኛታል።
12ጥበብ አንጸባራቂ ናት፤ ምንጊዜም አትደበዝዝም፤
ለሚያፈቅሯት በቀላሉ ትታያለች፤
ለሚፈልጓትም በቀላሉ ትገኛለች።
13ለሚሿት ሁሉ አስቀድማ ራሷን ታስተዋውቃለች፤
14እርሷን ፍለጋ ማልዶ የተነሣ፥ ችግር አያጋጥመውም፤
ጥበብን መሻት ጥበብን ማግኘት
15እርሷን ማሰላሰል ፍጹም ማስተዋል ነው፤
እርሷን ፍለጋ እንቅልፍ ያጣ፥ ከጥበቃ ፈጥኖ ይወጣል።
16የእርሷ የሆኑትን ሁሉ ትጠብቃቸዋለችና፤
በመንገዶቻቸው ላይ በቅንነት ትገለጥላቸዋለች፤
ሐሳቦቻቸውንም ታውቃለች።
17የጥበብ መነሻዋ ከልብ የመነጨ የመማር ፍላጐት ነው፤
የመማር ጉጉት እርሷን ማፍቀር ነው፤
18እርሷን ማፍቀር ማለት ሕጐቿን ማክበር ማለት ነው።
ሕጐቿን መጠበቅ አለመበላሸትን ማረጋገጥ ነው።
19አለመበላሸት ደግሞ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፤
20ስለዚህ ጥበብ መሻት ራስን ወደመግዛት ይመራል።
21እናንተ ነገሥታት ሆይ፥ ዙፋናችሁንና በትረ መንግሥታችሁን የምትወዱ ከሆነ፥
ጥበብን አክብሩ፤ አገዛዛችሁም ዘላለማዊ ይሆናል።
22የጥበብን ምንነትና አፈጣጠር ቀጥዬ አብራራለሁ፤ ምንም ምሥጢር አልደብቃችሁም፤ ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ዕድገቷን እገልጻለሁ፤ ስለ እርሷ የምናውቀውን ሁሉ ይፋ አደርጋለሁ፤ ከእውነት ግን አልርቅም።
23ከሚያቃጥል ምቀኝነት ጋር ወዳጅነት የለኝም፤ ምቀኝነትን ከጥበብ የሚያገናኝ ከቶውንም የለምና።
24የዓለም ደኀንነት የሚረጋገጠው፥ የጥበበኞች ቍጥር ሲበዛ ነው፤ የሕዝቦች ሰላምም እንዲሁ የሚረጋጠው፥ በንጉሡ ብልኀ አስተዳደር ነው። 25እንግዲያስ ከቃሌ ተማሩ፤ ጥቅሙም ለእናንተ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 6: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ