መጽሐፈ ጥበብ 17

17
አምስተኛው ተቃርኖ፦ ጨለማና የእሳት ዓምድ
1ፍርዶችህ ታላላቅና ድብቅ ናቸው፤
ያልተማሩ ነፍሶች ከመንገድ የወጡትም ለዚህ ነው።
2ክፉዎች ቅዱሱን ሕዝብ በኃይል ያንበረከኩ ቢመስላቸውም፥
በረጅሙ ሌሊት ከጣራቸው ስር ተተብትበው፥ ከዘላለማዊው ጥበቃ ተባረሩ።
3ከሠሯቸው ሥውር በደሎች ጋር ሳይታዩ ለማምለጥ ቢያስቡም፤
ጥቁሩ ዝንጉነት ጋርዷቸው፥ በጣረ ሞት ተሳቅቀው፥
በአስፈሪ ተስፋ መቁረጥ ተበታተኑ።
4መደበቂያ ብለው የያዙት ከለላቸው ፍርሃትን ሊያባርርለቸው አልቻለም፤
አስደንጋጭ ድምጾች በዙሪያቸው ያስተጋባሉ፤
ፊታቸው የጠቆረ ጐስቋላ መናፍስት ያስፈራሯቸዋል።
5የቱንም ያህል የሚነድ እሳት፥
በድምቀት የሚያበሩትም ከዋክብት ቢሆኑ ብርሃን ሊሰጧቸው አልቻሉም።
6ብቸኛው ብርሃናቸው፥ ድንገተኛው፥ አስፈሪውና ታላቁ
ያ ትርዒት በጠፋ ጊዜም ከፍርሃታቸው የነሣ
ምንም ጊዜ ካዩት ሁሉ እጅጉን አስደንጋጭ ሆነባቸው።
7በዚህ ጊዜ አስማታዊ ምትሃታቸው ኃይሉ ሁሉ ከዳው፤
አውቃለሁ ባይነታቸውም የማይጨበጥ ሆነ።
8ከታመሙ ነፍሶች ድንጋጤንና ፍርሃትን እናባርራለን ይሉ የነበሩ ሁሉ፥
በሚያስገርም ፍርሃት ተያዙ።
9የሚያስፈራ ነገር ባጠገባቸው ባይኖርም፥
የትናንሽ እንስሳት ሩጫና የአበቦች ፉጨት ያሸብራቸው ጀመር።
10ሊያመልጡት የማይችሉትን ነጻውን አየር እንኳን ለማየት አሻፈረን ብለው፥
በፍርናት ተቆራምደው ሞቱ።
11ክፋት በጣም ፈሪ ነው፤ ለዚህም ራሱን ያወግዛል፤
የኀሊና ተጽዕኖ ሲበዛበት ደገሞ ይብስበታል።
12ፍርሃት የአእምሮ እርዳታ መቋረጥ ከመሆን ውጭ ሌላ ሊሆን አይችልም፤
13በአእምሮህ ላይ ያለህ መተማመን ከቀነሰ፥
የጭንቀትህን ምክንያት አለማወቅህ የበለጠ አሳሳቢ ነው።
14እጅግ ደካማ የሆነውና እርሱኑ ከመሰለው የሲኦል ጉድጓድ የመነጨው
ጨለማ ሳይገፍ በአንድ ዓይነት እንቅልፍ ተሸንፈው ነበር።
15አሁን ደግሞ ግዙፍ መናፍስት ያባርሯቸዋል፥
ነፍሶቻቸውም በመደንገጣቸው ሽባ ሆነዋል፤
ድንገተኛና ያልተጠበቀ ሽብር አጥቅቷቸዋል።
16በዚያ የወደቀ ማንም ሰው ቢሆን፥
ካረፈበት ቦታ ተጣብቆ መዝጊያ በሌለው በዚህ እስር ቤት ይማቅቃል።
17ገበሬም ይሁን እረኛ፥ በበረሃም የሚሠራ ቢሆን፥
በድንገት እየተያዘ የወደቀበትን የማይታለፍ ዕጣ በግደ ይቀበላል፤
ሁሉም ባንድ የጨለማ ሠንሠለት ታሥረው ነበርና።
18የነፍሱ ፉጨት፥ እንደ ልብ በተዘረጉት ቅርንጨፎች ላይ ሆነው
ወፎች የሚያሰሙት ጣዕም ያለው ዜማ፥ የሚንፍዋፍዋው የወራጅ ውሃ ድምፅ፥
እየተምዘገዘጉ የሚወርዱ ዐለቶች ኳኳታ፥
19የማይታየው የሚቦርቁ እንስሳት መንገድ፥
ከዱር አራዊት የአስፈሪዎቹ ግሳት፥
ከተራሮች ላይ ካሉ ጉድባዎች የሚስተጋባው የገደል ማሚቶ፥
ሁሉም በፍርሃት ያሸማቅቃቸዋል።
20መላው ዓለም በቀን ብርሃን ደምቆ፥
ያለ ምንም ችግር ሥራውን ይሠራ ነበር።
21እነርሱ ላይ ብቻ ድቅድቅ ጨለማ ተንሠራፋ፤
የሚቀበላቸው ጽልመት ምስል ነው፤
እነርሱ ለራሳቸው ሸክም የሆኑትን ያህል፥ ጨለማው አልከበዳቸውም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ