መጽሐፈ ጥበብ 14
14
1እንደዚሁም ደግሞ ሞገደኛዉን የባሕር ማዕበል በመርከብ ለመሻገር የሚዘጋጅ ሰው፥
እርሱን ከተሸከመችው መርከብ እጅጉን ላነሰ የእንጨት ቁራጭ ልመናዉን ያቀርባል፤
2የእርሷ ግንባታ የመርከብ ሠራተኛውን ጥበብ ጠይቋል።
3እርሷን የሚመራት ግን፥ አባት ሆይ፥ ያንተ ጥበቃ ነው፤
አንተ በባሕር ውስጥ መንገድ፥ በማዕበሎችም መካከል መውጫ አበጅተሃል።
4ማንኛውም ዓይነት አደጋ ቢደርስ፥ አንተ ልታድነው እንደምትችል አሳይተሃልና፥
ልምድ የሌለው ሰው እንኳ በባሕር ላይ ሊጓዝ ይችላል።
5አንተ የጥበብህ ፍሬዎች እንዲባክኑ አትሻም፤
ከዚህም የተነሣ ሰዎች በትንሿ የእንጨት ስባሪ ተማምነው ማዕበሉን በታንኳ ያቋርጣሉ፤
እንዲያም ሆኖ ግን ካሰቡበት በደኀና ይደርሳሉ።
6ትዕቢተኞቹ ግዙፋን በጠፉበት በጥንት ዘመን፥
የዓለም ተስፋ በመርከብ ተጠለለ፤
በእጅህም እየተመራ የአዲሱን ትውልድ ዘር ለመጪው ዘመን አቆየ።
7የጽድቅ መሣሪያ የሆነው እንጨት የተባረከ ነው፤
8ሰው ሠራሹ ጣኦትና ቀራጩ ግን የተረገሙ ናቸው፤
ቀራጩ ጣኦትን በመሥራቱ፥ ጣኦቱ በስባሽ ቢሆንም እንኳ፥
አምላክ ተብሎ በመጠራቱ ርጉማን ናቸው፤
9እግዚአብሔር ክፉዎችንና ክፋትን እኩል ይጠላልና፤
10ሠራተኛውና ሥራው አንድ ዓይነት ቅጣትን ያገኛሉ።
11በእግዚአብሔር ፍጥረት ውስጥ አስጸያፊ፥ ለሰዎች ነፍስ ሐፍረት፥
ማስተዋል ለጐደላቸው ሰዎች እግሮችም ወጥመድ ሆነዋልና፥
ከዚህም የተነሣ የአሕዛብ ጣኦቶች እንኳን መጎብኘታቸው የማይቀር ነው።
የአምልኮተ ጣኣት አጀማመር
12ጣኦቶችን የመሥራት ሐሳብ የሴሰኝነት መጀመሪያ፥
የእነርሱም መታወቅ የሕይወት መጥፊያ ሆነ።
13በቀደመው ዘመን አልነበሩም፤ ዘላለማዊም አይደሉም።
14የሰው ግብዝነት እነርሱን ወደ ዓለም አመጣቸው፤
የተወሰነላቸውም አጭር ዕድሜ ነው።
15ያለ ዕድሜው በተቀጨ ልጅ ኀዘን
የትናንቱን ሬሣ ዛሬ ያመለከዋል፤
ምሥጢሩንና ሥርዓቱንም ለወገኖቹ ያስተላልፋል።
16ጊዜ ያልፋል፤ ባህልም ሕግ ይሆናል፤
17ሐውልቶች ይመለኩ ዘንድ ያዘዙ ገዢዎች ነበሩ፤
ከእነርሱ ርቀው የሚኖሩ በመሆናቸው በግንባር አክብሮታቸውን መግለጽ ላልቻሉት ሁሉ፥
የሚያከብሩትን ንጉሥ ምስል ያዩ ዘንድ፥ የገጽታው ንድፍ ተሠርቶ ይቀርብላቸው ነበር።
ዓላማውም ከዓይነ የራቀውን በቅርብ እንዳለ ማስመሰል ነበር።
18ገዢውን የማያውቁት ሰዎች እንኳን፥ በሠዓሊው ጥልቅ ስሜት በመገፋፋት፥
ለእርሱ ያላቸው አክብሬት እንዲስፋፋ ተደርጓል።
19የኋለኛው ገዢውን ለማስደሰት ሲል፥
ያለ ጥርጥር በሰው ጥበብ ሁሉ በመጠቀም፥
ከእውነተኛው ገጽታ የተዋበ ምስል አቅርቧል።
20ሕዝቡም በምስሉ ውበት ተታልሎ እንደ ሰው ያከበረውን፥
እንደ አምላክ ያመልከው ጀመር።
21በዚህ ዓይነት በመጥፎ ዕድል ወይም በኃይል ተፅዕኖ
የከበረውን የእግዚአብሔር ስም ለድንጋይና ለእንጨት በሰጡ ጊዜ
የሰዎች ሕይወት በወጥመድ ገባች።
የአምልኮተ ጣኦት ውጤት
22እነርሱ ስለ እግዚአብሔር ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት ይኸው ብቻ አልነበረም፤
አላዋቂነት የወለደውን አስፈሪ የፍልሚያ ሕይወት እየመሩ፥
መቅሰፍቶቹን ሰላም ብሎ ይጠሯቸዋል።
23ሕፃናትን የሚገድሉበት ሥርዓታቸው፥ መናፍስታዊ ምሥጢራቸው፥
ወይም የእብደት ሞፈራቸው፥ እንግዳ ባህላቸው፥
24እንደሚያመለክቱት በአኗኗሯቸው ወይም በጋብቻዎቻቸው የቀራቸው ንጹሕና ጨርሶ የለም።
አንዱ ሌላውን በተንኮል ሲገድል፥ ወይም ከሚስቱ ጋር ሲሴስን ይታያል።
25የትም ቦታ በደም የተጨማለቀ ግድያ፥ ሌብነትና ማጭበርበር፥
ጉቦ፥ ውስልትና፥ ዓመጽ፥ የሐሰት ምስክርነት፥
26ሰላማዊ ሰዎችን መበጥበጥ፥ ወሮታ ቢስ መሆን፥
ነፍስን ማሳደፍ፥ በተፈጥሮ ላይ ማመፅ
ጋብቻን ማፋለስ፥ አመንዝራነትና ተስፋ መቁረጥ ይታያል።
27ስማቸው ሊነሳ የማይገቡ ጣኦቶችን ማምለክ፥
የክፋት ሁሉ ምክንያት መነሻው፥ ማክተሚያውም ነውና።
28ጣኦቶችን የሚያመልኩ ሰዎች፥ ፈንጠዝያቸው እስከ እብደት ይደርሶል፤
ወይም ትንቢታቸው ሐሰት ነው፤ በክፋትም ይኖራሉ፤
አልያም ያለ ማመንታት በሐሰት ይምላሉ።
29የሚያምኑት ሕይወት በሌላቸው ጣኦቶት ስለሆነ
የሐሰት መሐላዎቻቸው ሊጐዷቸው እንደሚችሉ አልተገነዘቡም።
30ለዚህ ድርብ ወንጀል ግን ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ፥
ጣኦቶችን በማምለክ እግዚአብሔርን አዋርደዋልና፤
ቅድስናውንም በመናቅ በተንኮል የሐሰት መሐላ አድርገዋልና።
31የክፉ ሰዎችን በደል የሚከታተሉት፥ የሚምሉባቸው ጣኦቶች ሳይሆኑ፥
ለኃጡአተኞች የተወሰነው ቅጣት ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 14: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ