መጽሐፈ ጥበብ 15
15
የእስራኤል ሕዝብ በጣኦት አያመልክም፥
1አንተ አምላካችን ግን ደግና እውነተኛ፥ በቶለ የማትቆጣ፥
ዓለምን በምሕረትህ የምትገዛ ነህ።
2ብንበድል እንኳ እኛ ያንተ ነን፤ ሥልጣንህንም እንቀበላለን፤
ግን ያንተ መሆናችንንም ስለምናውቅ አንበድልም።
3አንተን ማወቅ ፍጹም ቀናነት ነው፤
ጌትነትህን መቀበል ሕያው ሆኖ የመኖር መሠረት ነው።
4ያለ ቦታቸው በዋሉ የሰው ልጅ ጥበብ ግኝቶች፥
ወይም በሠዓሊዎች ፍሬቢስ የፈጠራ ሥራዎች፥
5ሞኞችን በሚያማልሉ ግዑዝና ትንፋሽ አልባ ምስሎችም አልተታለልንም።
6እነርሱን የሚሠሩ፥ እነርሱን የሚሹ፥ እነርሱንም የሚያመልኩ፥
የክፋት ወዳጆችና እንደነዚህ ላሉ ፍሬቢስ ተስፋዎች የተገቡ ናቸው።
ጣኦት ቀራጮች አላዋቂዎች ናቸው
7ሸክላ ሠሪው ለስላሳውን አፈር ለውሶ፥
ቀርጾና ደክሞ እኛ የምንገለገልባቸውን ቁሳቁሶች ይሠራል፤
ለከበረ ዓላማ የሚውለውን ዕቃ ለረከሰውም ቢሆን እንዲሁ የሚሠራው ከዚያው ጭቃ ነው።
ከሁለቱ ግልጋሎቶች የትኛው ለየትኛው እንደሚውልም የሚወስነው እርሱ ነው።
8ከንቱ ድካም እርሱ ራሱ በቅርቡ ከወጣበት አፈር፥
ብዙም ሳይቆይ የተዋሳትን ነፍስ እንዲመልስ በተጠየቀ ጊዜ
ከሚገባበት ምድር፥ ከዚያው ጭቃ ፍሬ ቢሱን ጣኦት ቀረጸ።
9ከዚህ ሁሉ በኋላም ስለ ሞቱ፥ ስለ ዕድሜው ማጠርም አይጨነቅም፤
ነገር ግን ከወርቅ ሠሪዎችና ክብር አቅላጮች ጋር ይፎካከራል፤
የነሐስ ሠራተኞችን ለመምሰል ይጥራል፤
አስመስሎ በመሥራቱም ይታበያል።
10ልቡ አመድ፥ ተስፋው ከምድር የከፋ፥
ሕይወቱ ከጭቃ ይልቅ የተናቀ ነው።
11ሕያው ነፍስ እፍ ያለበትን፥
የማይሞት መንፈስ የሰጠውን፥
አንዱን ፈጣሪውን ዘንግቷል።
12ከዚህም በላይ ሸክላ ሠሪው ሕይወታችንን የሚያያት እንደ ጨዋታ ነው፤
ምድራዊ ቆይታችንንም ውጣ ውረድ እንደሚበዛበት ትርዕይት ይቆጥረዋል።
13እርሱ ከማንም የበለጠ መበደሉን ራሱ ያውቀዋል፥
ከአንድ ዓይነት አፈር ተሰባሪ ሸክላና ጣኦቶችን የሚሠራ ነውና።
የግብጻውያን ታላቅ ስሕተት፥ ገደብ የለሹ አምልኮተ ጣዖት
14የመጨረሻዎቹ ሞኞች ከሕጻን ልጅ ነፍስም በበለጠ ሊታዘንላቸው የሚገቡ፥
የሕዝብ ጠላቶችና ባንድ ወቅት በአምባገነንነት ይጨቁናቸው የነበሩት ናቸው።
15የአረማውያኑን ጣእቶች ሁሉ አማልክቶቻቸው አደጉ፤
እነርሱ ለማየት ዓይናቸውን፥ ለመተንፈስ አፍንጫቸውን፥
ለመስማት ጆሮዋቸውን፥ ለመጨበጥ ጣቶቻቸውን፥
ለመራመድም እግሮቻቸውን መጠቀም አይትሉም።
16ጣኦቶቹ የተሠሩት በሰው፥ እስትንፋሱን በውሰት ባገኘ ፍጡር ነው።
ማንም ሰው ራሱን የመሰለ ጣኦት ከቶ ሊቀርጽ አይችልም።
17ሞት ዕጣ ፈንታው ነውና ያልተባረኩት እጆቹ ሊሠሩ የሚችሉት በድን ብቻ ነው።
ከሚያመልካቸው ጣኦቶች ይልቅ፥ እርሱ የከበረ ነው፤
እርሱ መኖር ይችላል፥ እነርሱ ግን ፈጽሞ ሊኖሩ አይችሉም።
18እጅግ የሚያስቀይሙትን እንስሳት ያመልካሉ፤
አእምሮ ቢስነታቸውም ከሌሎቹ ሁሉ የባሰ ነው።
19እንስሳትን ተወዳጅ የሚያደርጋቸው ውበታቸው ከሆነ፥
ከቶውንም የማይስቡ የእግዚአብሔርን ቡራኬና ምርቃትም ያላኙ ናቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 15: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ