መጽሐፈ ሲራክ 34

34
1 # ዘዳ. 13፥1-5፤ 18፥9-14። ከንቱና የማይጨበጥ ተስፋ የሞኞች ነው፤ ሕልሞችም ለእንርሱ ክንፍ ይሰጧቸዋል። 2ሕልሞችን ማመን ጥላን እንደ መጨበጥና ነፋስን እንደማባረር ነው። 3ሕልሞች ከመስተዋቶች አይለዩም፤ የፊትህ ነጸብራቅ መልሶ ያይሃል። 4ባለመንጻት የሚነጻ፥ በሐሰትስ የሚረጋገጥ ምንድነው? 5ጥንቆላ፥ ገድና ሕልም፥ እንደ ነፍስ ጡር ቅዠት አይጨበጡም። 6ከልዑል እግዚአብሔር ካልተላኩ በቀር አትጨነቁላቸው። 7እነርሱን ያመኑ ብዙዎች ጠፍተዋል፤ ተስፋቸውንም በእነርሱ ላይ ያደረጉ ሰዎች ኀዘን ላይ ወድቀዋል። 8ሕጉን መፈጸም ግን ይህን የመሰለ ሐሰት አይሻም፤ ጥበብም ስለ ትክክለኛነቷ ፍጹም ናት። 9ብዙ ቦታዎችን ያዩ ብዙ ያውቃሉ፤ ልምድ ያለው ሰው የሚናገረውም ከመሬት አይወድቅም። 10ያልተፈተነ ሰው ዕውቀቱ ጥቂት ነው፤ ተጓዥ ሰው ግን ሁሉንም ያውቃል። 11በጉዞዎቼ ላይ ብዙ ነገር አየሁ፤ በቃላት ከምገልጸውም በላይ ተገነዘብሁ። 12ብዙ ጊዜ የሞት ጥላ አንዣቦብኛል፤ ይሁን እንጂ ተርፌያለሁ። ምክንያቱም እንዲህ ነው፥ 13እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች መንፈስ ሕያው ነች። 14እግዚአብሔርን የሚፈራ ከቶውንም ሊጠራጠር አይገባም፤ ተስፋውም በጌታ ነውና አይፈራም። 15እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነፍስ ትደሰት፤ የሚተማመነው በማነው? ረዳቱስ ማነው? 16እርሱን የሚወድትን ሁሉ የአምላክ ዐይኖች ይከታተላሉ። የማይደፈረው ጠባቂያቸው፥ ጠንካራውም ደጋፊያቸው እርሱ ነው። የበረሃው ነፋስ ከለላ፥ የቀን ሐሩር ጥላ፥ ከመከራ ጠባቂ፥ ከውድቀታቸውም አዳኛቸው ነው። 17እርሱ መንፈስን ያድሳል፤ ዐይኖችን ያበራል፤ ጤና፥ ሕይወትንና በረከትን ይሰጣል።
መሥዋዕቶች
18ፍትሕን በማጓደል የተገኘውን ስጦታ፥ በመሥዋዕትነት ማቅረብ ማላገጥ ነው። የክፉ ሰው ስጦታዎች ተቀባይነት አይኖራቸውም። 19ልዑል እግዚአብሔር ከበደለኞች በሚቀርቡ ስጦታዎች ደስ አይሰኝም፤ የመሥዋዕቶች ብዛት ኃጢአትን ይቅር አያሰኝም። 20ከድሆች ሀብት ተነጥቆ የሚቀርብ መሥዋዕት፥ ልጁን በአባቱ ፊት እንደ መሠዋት የከፋ ነው። 21ቁራሽ እንጀራ የችግረኞች ሕይወት ነው፤ ከአፋቸው ላይ እርሷኑ መንጠቅ ነፍስ ማጥፋት ነው። 22የሰውን መተዳደሪያ መንጠቅ ያው መግደል ነው፤ 23አንዱ ቢያፈርስ፥ ሌላው ቢገነባ፥ ከድካም በቀር ምን ያተርፋሉ? 24አንደኛው ሲጸልይ ሌላኛው ቢራገም፥ ጌታ የሚያደምጠው የትኛውን ነው? 25አንዱ ሬሳ ነክቶ እጁን ቢታጠብ፥ ዳግመኛም ቢነካው የመታጠቡ ትርጒም ከምኑ ላይ ነው? 26ለኃጢአት ስርየት የሚጾም ሰው፥ ዳግም የሚበድል ከሆነም እንዲሁ ነው። የዚያን ሰው ጸሎት ማን ይሰማዋል? ራስን ማዋረድ ምን ይጠቅማል?

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ