መጽሐፈ ሲራክ 16
16
የግትሮች ዕጣ
1የማይረቡ ብዙ ልጆች አትመኝ፤ በክፉ ልጆች አትደሰት። 2ምንም ያህል ቢበዙ ፈሪሃ እግዚአብሔር ካላደረባቸው ያብራክህ ክፋዮች በመሆናቸው ብቻ አትደሰት። 3ረጅም ዕድሜ ይኖራቸዋል ብለህ አትጠብቅ፤ በቁጥራቸውም ብዛት እምነት አይኑርህ፤ ከሺህ አንድ የተሻለ ይመረጣል፤ ክፉዎች ከመውለድ ያለ ዘር ማለፍ ይቀላል። 4አንድ አስተዋይ ከተማዋን በሰው ይሞላታል፤ የሕገ ወጥ ሕዝቦች ዘር ግን ይደመሰሳል። 5ይህን የመሰሉ ሁናቴዎች ዐይኖቼ አይተዋል፤ በጣም የሚገርሙ ነገሮችን ጆሮዎቼ ሰምተዋል። 6በኃጢአተኞች ማኀበር እሳት ይንቀለቀላል፥ በማይታዘዝ ሕዝብ ላይ ቁጣ ይነዳል። 7#ዘፍ. 6፥4፤ ጥበ. 14፥6።ጥንታውያኑን ግዙፎች እግዚአብሔር ይቅርታ አላደረገላቸውም፤ በኃይላቸውም ተኩራርተው በእርሱ ላይ አምፀዋልና። 8ከሎጥ ጋር የሚኖሩትን ሰዎች አልሳሳላቸውም፤ በትዕቢታቸው ምክንያት ጠላቸው። 9በኃጢአታቸው የተኩራሩ የጥፋት ሕዝቦችን አልራራላቸውም፤ 10በልበ ደንዳናነታቸው በአንድ ላይ የተሰበሰቡትን ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ተጓዦችን እንኳ አላዘነላቸውም። 11የቀረው ግትር ሰው አንድ ሆኖ፥ እርሱም ሳይቀር አምልጦ ቢሆን ኖሮ፥ የሚያስደንቅ ይሆን ነበር። ምሕረትና ቁጣ የእግዚአብሔር ናቸው፤ ይቅርታ ሊያደርግ ወይም ሊጠፋ ሥልጣን ያለው እርሱ ብቻ ነው። 12ምሕረቱ ታላቅ እንደሆነ ሁሉ፥ ኃያልነቱ አስፈሪ ነው። ሰዎችን እንደ ሥራቸው ይፈርዳል። 13ኃጢአተኛ በተንኮል ካገኘው ጥቅም ጋር አያመልጥም፤ የጻድቁም ትዕግሥት ያለ ዋጋ አይቀርም። 14መልካም ሥራን ሁሉ ይመለከታል፤ እያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው ዋጋውን ያገኛል።#16፥14 ሌሎች የጥንት ጽሑፎች ቍጥር 15-16 እንደሚከተለው ያነቡታል፦ 15. ከሰማይ በታች ሥራው የተገለጠውን እሱን እንዳያውቀው፥ እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አደነደነው፤ 16. ምሕረቱ በፍጥረታቱ ሁሉ የታወቀ ነው፤ ብርሃንና ጨለማም ለሰው ልጆች ሰጥቷቸዋል።
የቅጣት አይቀሬነት
17“ከእግዚአብሔር እሸሸጋለሁ፥ እዚያ ላይ ሆኖ ማን ያስታውሰኛል፤ ከብዙ ሰው መካከል እኔ አልለይም፤ በፍጥረትስ ዐይን ኢምንት አይደለሁምን?” አትበል 18ሰማይ፥ ከሰማይም በላይ ያሉ ሰማያት፥ መሬትና እልም ያለ ጥልቀትም እርሱ በመጣ ጊዜ እንደሚንቀጠቀጡ ተመልከት። 19ተራሮችና የምድር መሠረቶች እሱ ሲመለከታቸው በፍርሃት ይርዳሉ። 20ግን ይህን ሁሉ ሰዎች አያስቡትም፤ የሱን መንገዶች በጥንቃቄ የሚያስተውላቸው ማን አለ? 21ማንም ሊያየው እንደማይችለው የነፋስ ማዕበል፤ አብዛኛዎቹ ሥራዎቹ ድብቅ ናቸው። 22የጽድቅ ሥራዎቹን ማን ያበሥራል? ማንስ ይጠብቃቸዋል? የተስፋው ቃል በጣም ሩቅ ነው። 23ደካማ አስተሳሰቦች ያለው ሰው፥ የማይረባ፥ ከትክክለኛው መንገድ የወጣ፥ በመሳሳቱ የማይቆጭ ሰው አመለካከት ይህን ይመስላል።
ሰዎች በፍጥረት ዓለም
24ልጄ ሆይ አድምጠኝ፥ ዕውቀትንም አግኝ፥ ልብህን በቃሎቼ ላይ አድርግ። 25ሥርዓትን በዘዴ፥ እውቀትንም በትክክል አሳይሃለሁ። 26ጌታ በመጀመሪያ ሥራዎቹን በፈጠረ ጊዜ፥ ለሁሉም ቦታቸውን ሰጥቷቸዋል። 27ሥራዎቹን ለሁልጊዜ፥ ከመነሻ እስከ መጨረሻ ሐረጋቸው ድረስ ወስኗል፤ ረኃብና ድካም አያውቁም፤ ተግባራቸውንም አይዘነጉም። 28አንዱ በሌላው ሕይወት ከቶውንም ገብቶ አያውቅም፤ የፈጣሪውን ቃል የማይፈጽም የለም። 29ከዚህ በኋላ ጌታ ወደ ምድር ተመለከተ፤ ምድርን በመልካም ሥራው ሞላት። 30የምድርን ገጽ በሁሉም ዓይነት እንስሳት ሸፈናት፤ ሁሉም ወደ እርሷው ይመለሳሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 16: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ