መጽሐፈ ሲራክ 15

15
1እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ይህን ሁሉ ያደርጋል፤ ሕግን አጥብቆ የሚይዝ ጥበብን ያገኛል። 2ጥበብ እንደ እናት ሆና ልታገኘው ትመጣለች፤ እንደ ድንግል ሙሽራ ሆና ትቀበለዋለች። 3የዕውቀት እንጀራ ታቀርብለታለች፤ የጥበብን ውሃ ታጠጣዋለች። 4እርሱም እርሷን ይደግፋል፥ አይወድቅምም፥ በእርሷ ይተማመናል፥ አያፍርም። 5ከባልንጀሮቹ በላይ ከፍ ታደርገዋለች፥ በስብሰባ መካከል እንዲናገር አፉን ትከፍትለታለች። 6ደስታና የደስታ አክሊል ይቀበላል፤ ዘላለማዊ ስምም ይወርሳል። 7አላዋቂዎች ግን አያገኟትም፥ ኃጢአተኞች አያዩዋትም። 8ከትዕቢተኛ ትርቃለች፤ ሐሰተኞች አያስታውሷትም። 9ከኃጢአተኛ አፍ ምስጋና አይጠበቅም፤ ጌታ በዚያ አላኖረውምና። 10ምስጋና በጥበብ ይነገራል፤ የሚያነሳሳውም እግዚአብሔር ነው።
የምርጫ ነጻነት
11 # ሲራ. 17፥1-12። የሚጠላውን አይፈጥርምና ኃጢአት እንድሠራ ምክንያት የሆነኝ ጌታ ነው አትበል። 12እግዚአብሔር ሐሳቡን ለመፈጸም ኃጢአተኛ እንዲረዳው አያስፈልገውምና፥ ኃጢአት እንድሠራ ያደረገኝ እሱ ነው አትበል። 13ጌታ ክፉ ነገርን ሁሉ ይጠላል፤ እርሱን የሚፈራም ክፋትን አይወድም። 14በመጀመሪያ ሰውን የፈጠረ እሱ ነው፤ ሰው በገዛ ሐሳቡ እንዲመራ ተወው። 15ከፈለግህ ትእዛዛቱን ታከብራለህ፤ ለእርሱም ፈቃድ ትታመናለህ። 16ከፊትህ እሳትና ውሃ አስቀምጧል፤ በምትሻው ውስጥ እጅህን ጨምረው። 17ለሰዎች ሕይወትና ሞት ቀርበውላቸዋል። ለእያንዳንዱም ሰው የመረጠው ይሰጠዋል። 18የጌታ ጥበብ ሰፊ ነውና፥ እርሱ ኃያልና ሁሉን የሚያይ ነው። 19ዐይኖቹም የሚመለከቱት ወደሚፈሩት ሰዎች ነው፤ እሱ የሰዎችን ሥራ ሁሉ ያውቃል። 20ሰው ክፉ እንዲሆን አላዘዘም፥ ሰው ኃጢአት እንዲሠራ አልፈቀደም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ