መጽሐፈ ሲራክ 14
14
እውነተኛ ደስታ
1በንግግሩ ያልተሳሳተ ሰው፥ ስለ ኃጢአትም መጸጸት የማያስፈልገው የተባረከ ነው። 2ኀሊናው የማይወቅሰውና በተስፋ የኖረ ሰው የተባረክ ነው። 3ለንፉግ ሃብት አይገባውም፤ ለቀናተኛስ ንብረት ምን ያደርግለታል? 4በመስቀንቀን ሃብት የሚያከማች ለሌሎች ያጠራቅማል፤ እነርሱም በእርሱ ሃብት ይንደላቀቃሉ። 5ለገዛ ራሱ ክፉ የሆነ ማንን ይጠቅማል? የራሱ የሆነውን እንኳ አይደሰትበትም። 6የገዛ ራሱን ከሚጐዳ ሰው የባሰ ክፉ አይገኝም፤ እነሆ የክፋቱን ዋጋ እንደዚሁ ያገኛል። 7ደግ እንኳ ቢሠራ ፈቅዶ የሚያደርገው አይደለም፤ በመጨረሻም ክፋቱ ይገለጥበታል። 8ቀናተኛ ዐይን ያለው ሰው መጥፎ ነው፤ ስለሌሎች ሕይወት አይጨነቅም፤ ፊቱንም ይመልስባቸዋል። 9የንፉግ ሰው ዐይን ባለው አይረካም፤ ንፍገትም ነፍሱን ያኮማትራታል። 10ንፉግ ሰው ለእንጀራ ይሳሳል፤ በማዕዱም ጥጋብ የለም። 11ልጄ ሆይ በሚቻልህ መጠን ራስህን በመልካም አስተዳድር፤ ለእግዚአብሐርም የተገባውን መባ አቅርብ። 12ሞት ሳትዘገይ እንደምትመጣ አስታውስ፤ የሲኦልን ውል አይተህ አታውቅምና፤ 13ከመሞትህ በፊት ለወዳጅህ ደግ ነገር አድርግለት፤ እንደተቻለህ በደግነት አስተናግደው። 14የዛሬው ደስታ አያምልጥህ፤ ከተገቢው ደስታ ድርሻህ አያምልጥህ። 15የደከምህበትን ፍሬ ለሌላ ትተወው የለምን? የድካምህን ፍሬ ዕጣ እንዲጣጣሉበት ታደርግ የለምን? 16ስጥ፥ ተቀበልም፥ ራስህን አስደስት፤ በሲኦል የሚገኙ ደስታዎች የሉምና። 17እንደ ልብስ ሁሉ ሥጋም ያረጃል፤ ቋሚው ሕግ “ሁሉም ይሞታል” የሚለው ነው። 18ቅርንጫፉ በበዛ ዛፍ ላይ እንደሚበቅል ቅጠል፥ አንዳንዶቹ ይወድቃሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ያድጋሉ፤ የሥጋና የደም ትውልዶች እንደዚሁ ናቸው፤ አንዱ ሲሞት ሌላው ይወለዳል። 19ሰው የሠራው ነገር ሁሉ ይበሰብሳል፥ ይጠፋል፤ ሰሪውም እንዲሁ ያልፋል።
የጠቢቡ ደስታ
20 #
ምሳ. 8፥32-35። ጥበብን የሚማርና አእምሮው እንዲመራመር የሚያደርግ ሰው የተባረከ ነው። 21በልቡ የጥበብን መንገድ የሚያሰላስልና ምሥጢሯንም ጠልቆ የሚመረምር እርሱ የተመረቀ ነው። 22እንደሚያድን ሰው ይከተላታል፥ በመንገዷም አድፍጦ ይጠብቃል፤ 23በመስኮቶችዋም ይቃኛል፤ በደጃፍዋ ሆኖ ያዳምጣል። 24በቤትዋም አጠገብ ይቀመጣል፤ ችካሉንም በግንቦቿ ሥር ይተክላል። 25በአጠገቧ ድንኳኑን ይተክላል፤ ውብ በሆነም ስፍራ ይኖራል። 26ልጆቹን በእርሷ ጥላ ሥር ያስቀምጣል፤ ከቅርንጫፎቿም በታች ይኖራል። 27ከሐሩሩ ይጠለልባታል፤ በሞገሷም ቤቱን ይሠራል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 14: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ