መጽሐፈ ሲራክ 13
13
ከእኩዮችህ ጋር ዋል
1ቅጥራን የሚነካ ያድፋል፤ ከትዕቢተኛም ጋር የሚውል እርሱን ይመስላል። 2ከአቅምህ በላይ የሆነን ሸክም ለማንሳት አትሞክር፤ ከአንተ የበለጠ ኃያልና ሃብታም ከሆነው ጋር አትጎዳኝ፤ ስለምን የሸክላውን ማሰሮ ከብረት ድስት ጎን ታኖራልህ? ሁለቱ ሲጋጩ ይሰበራልና። 3ሀብታም በድሎ ይቆጣል፤ ድኃ ተበድሎ ይቅርታ ይለምናል። 4ከጠቀምከው ይገለገልብሃል፤ ካጣህ ይተውሃል። 5ገንዘብ አለህን? ካለህ ከአንተ ጋር ይኖራል፤ ያለምንም አስተያየት ባዶ ያስቀርሃል። 6ታስፈልገዋለህ? ከሆነ ያታልልሃል፥ ይስቅልሃል፥ ተስፋም ይሰጥሃል፥ በትሕትና ያናግርሃል፥ ምን ላድርግልህ? ብሎ ይጠይቅሃል። 7በራት ግብዣው ላይ ያዋርድሃል፥ ሁለቱ ወይም ሦስቱ ያለህን ካሟጠጠ በኋላ ይስቅብሃል፤ ከዚህ በኋላ ባየህ ቍጥር ፊቱን ይመልስብሃል፥ ራሱን ይነቀንቅብሃል። 8እንዳትታለል ተጠንቀቅ፤ በሞኝነትህ እንዳትዋረድ እራስህን ጠብቅ። 9ሹም ሲጋብዝህ ቸልተኛ ምሰል፤ እርሱም ግብዣውን ደጋግሞ ያቀርብለሃል። 10እንዳይገፋህ አትጣደፍ፤ እንዳይረሳህ አትራቅ፤ 11እንደ አቻህ አትቅረበው፤ የቃላቱንም አወራረድ አትመን፤ ምክንያቱም ንግግሩ አንተን መፈተኛ ነው፤ በወዳጅነት ሽፋንም ይመዝንሃል። 12ወሬ ቸርቻሪ ምሕረት የለውም፤ አንተን ከመደብደብና ከማሰር አይቆጠብም። 13ተጠበቅ፥ በጣም ተጠንቀቅ፤ የምትጓዘው ከውድቀትህ ጋር ነውና። 15ሕይወት ያለው ፍጥረት ሁሉ መሰሉን፥ ሰው ሁሉ ባልንጀራውን ይወዳል። 16ሁሉም ፍጡር ከመሰሉ ጋር ይቀላቀላል፤ ሰዎችም ከመሰሎቻቸው ጋር ይቀራረባሉ። 17ተኩላና በግ ምን አንድነት አላቸው? ኃጢአተኛም በጻድቅ ፊት እንዲሁ ነው። 18በጅብና በውሻ መሀል ምን ሰላም ይገኛል? በሀብታምና በድኃ መሐልስ እንዲሁ አይደለምን? 19የሜዳ አህዮች በበረሃ የአንበሶች ግዳይ ናቸው፤ ድሆችም እንዲሁ የሀብታሞች ሰለባ ናቸው። 20ትዕቢተኞች ትሕትናን እንደሚጠሉት ሁሉ፥ ሀብታሞችም ድሆችን እንዲሁ ይጠላሉ። 21ሀብታም ሲወድቅ ወዳጆቹ ይደግፉታል፤ ድኃ ሲወድቅ ወዳጆቹ ይገፉታል። 22ሀብታም ሲያዳልጠው የሚይዙት እጆች በርካታ ናቸው። ንግግሩ ፍሬቢስ እንኳ ቢሆን ያደንቁለታል፤ ድኃው ሲያዳልጠው ይነቀፋል፤ መልካም ነገር ቢናገም ቦታ የሚሰጠው የለም። 23ሀብታም ሲናገር ሁሉም ያዳምጣል፤ ንግግሩንም ከፍ ከፍ ያደርጉለታል። ድኃ ሲናገር ይህ ማነው ይባላል፤ ቢደናቀፍም ገፍተው ይጥሉታል። 24በደለኞች “ኃጢአት በሌለበት ሀብት ጥሩ ነው፤ ድህነት ግን መጥፎ ነው” ይላሉ። 25በደግም ሆነ በክፉ የሰውን ገጽታ የሚቀይረው ልቦናው ነው። 26ፈገግታ የሞላበት ገጽታ የደስተኛ ልብ ምልክት ነው። ምሳሌዎችን መፍጠር ግን አድካሚ ሥራ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 13: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ