መጽሐፈ ሲራክ 12
12
የደግነት ሕግጋት
1 #
ማቴ. 7፥6። ደግ ነገር ስታደርግ ለማን እንደምታደርገው ዕወቅ፤ ደግ ሥራዎችህ በከንቱ አይቀሩም። 2ለጻድቅ ሰው መልካምን አድርግ፤ ዋጋህን ታገኛለህ፤ 3በክፉ ነገር ጸንቶ የሚኖር ሰው ደስታ አያገኝም፤ ምጽዋት ማድረግ የማይፈልግ ደስታ የለውም። 4ለጻድቅ ሰው ስጥ፤ ግን ኃጢአተኛን ከቶ አትርዳ። 5ለትሑት ሰው ደግ አድርግ፥ ለክፉ ሰው ምንም አትስጥ፤ እንጀራም ከልክለው፥ ምንም አትስጠው፥ ከሰጠኸው ግን በአንተ ላይ ኃይል ያገኛል፤ ባደረግህለት ደግ ሥራ ሁሉ ዕጥፍ ክፋት ያደርግብሃል። 6ልዑል እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ይጠላል፤ ለክፉዎች የሚገባቸውን ቅጣት ይሰጣቸዋል። 7ለደግ ሰው ስጥ፤ ኃጢአተኛን ግን አትርዳ።
እውነተኛና ሐሰተኛ ወዳጅ
8በደስታ ጊዜ ትክክለኛ ወዳጅን መለየት አትችልም፤ በመከራ ጊዜ ግን ጠላትህን አትስተውም። 9አንድ ሰው ሲሳካለት ጠላቶቹ ይሆናሉ፤ ሁሉም ነገር ሲበላሽበት ደግሞ ወዳጁ እንኳ ይርቀዋል። 10ጠላትህን ከቶ አትመነው፤ ነሐስ እንደሚዝግ፥ የጠላትህም ተንኮል እንደዚያው ይሆናል። 11ትሑት ቢመስልና አንገቱን ቢደፋም፥ ቁጥብነትህን ግፋበት፤ ጥንቃቄም አድርግበት፥ በሱ ዘንድ መስተዋት እንደሚወለውል ሁን፤ ዝገቱም እስከ መጨረሻም እንደማይዘልቅ እወቅ። 12ከአጠገብህ አታስቁመው፤ ገፍትሮህ ቦታህን ሊይዝ ይችላልና፤ ወንበርህን እንዳይቀማህ በቀኝህ አታስቀምጠው፤ የንግግሬን ትክክለኛነት በመጨረሻ ትገነዘበዋለህ፤ በመጸጸት ቃሎቼን ታስታውሳቸዋለህ። 13በእባብ ለተነከሰው አስማተኛ፥ ከጨካኝ አውሬዎችስ ጋር ለሚውል ማን ያዝንለታል? 14የኃጢአተኛን ወዳጅ የሚሆንና ተባባሪውም የሚሆን እንዲሁ ነው። 15ለአጭር ጊዜ ከአንተ ጋር ይቆያል፤ መንገድ ከከፍትክለት ግን ጥቅሙን ያሳድጋል። 16ጠላት ንግግሩ ጣፋጭ ሊሆን ይችላል፤ ልቡ ደግሞ አንተን ወደ ጉድጓድ የሚጥልበት ውጥን ይዟል። የአዞ ዕንባ ሊያነባ ይችላል፤ አጋጣሚውን ካገኘ ግን የደም ጥሙ አይረካም። 17መከራ ቢወድቅብህ ከፊትህ ቀድሞ ይገኛል፤ የሚረዳህም መስሎ ያደናቅፍሃል። 18ራሱን ይነቀንቃል፤ ያጨበጭባል፤ ብዙ ያንሾካሹካል ገጹም ይለወጣል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 12: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ