መጽሐፈ ሲራክ 11
11
የመልክ አታላይነት
1ጥበብ ደሃውን ታኰራዋለች፤ ከታላላቆችዋ ጋር ታስቀምጠዋለች፤ 2ስለ ውበቱ ማንንም አታመስግን፤ በመልኩ ማንንም አትጥላ። 3ከበራሪ ፍጡራን ታናሺቱ ንብ ናት፤ ምርቷ ግን ከጣፋጮች ጣፋጭ ነው። 4ሰዎች ሲያከብሩህ አትኩራ፤ የእግዚአብሔር ሥራዎች ድንቅ ነገር ግን ለሰዎች ድብቅ ናቸው። 5በርካታ ነገሥታት ተዋርደው በምድር ላይ ተቀመጠዋል፤ ያልተጠበቀው ሰውም ዘውድን ተቀዳጅቷል። 6ብዙ ባለ ሥልጣኖች በፍጹም ተዋርደዋል፤ ዝነኞች የነበሩ ሰዎች በሌሎች እግር ሥር ወድቀዋል።
ማመዛዘንና ማሰላሰል
7ጉዳዩን ከመገንዘብህ በፊት ሰውን አትንቀፍ፤ አስቀድመህ አስብ፤ በኋላ ንቀፍ። 8መልስ ከመስጠትህ በፊት አድምጥ፤ በሰው ንግግር መካከል ጣልቃ አትግባ። 9በማያገባህ ጉዳይ አትከራከር፤ በኃጢአተኞች ፀብ ውስጥ አትግባ። 10ልጄ ሆይ ከአቅምህ በላይ ሥራ አታብዛ፤ ፍላጎቶችህ ቢበዙ ስለ እነርሱ ትቸገራለህ፤ ብትሮጥም አትደርስም፤ ብትሸሽም አታመልጥም። 11አንዳንዶች በፍጥነት ጠንክረው ይሠራሉ፤ እራሳቸውን የሚያገኙት ግን ጭራ ሆነው ነው።
በእግዚአብሔር ብቻ እመን
12አንዳንዶች እርዳታ የሚሹ ደካሞች ናቸው። ንብረት የሌላቸው እና በድኀነት የበለጸጉ ናቸው። እግዚአብሔርም ዐይኑን ወደ እነርሱ ይመልሳል። ከገቡበትም አዘቅት ያወጣቸዋል። 13ራሳቸውን ቀና ያደርግላቸዋል፤ ብዙዎች በነሱ ይደነቃሉ፤ 14ጥሩና መጥፎ፤ ሕይወትና ሞት፤ ድኀነትና ሀብት ሁሉም ከእግዚአብሔር የሚገኙ ናቸው። #11፥14 በአንዳንድ ቅጂዎች ውስጥ እንደሚከተለው ይነበባ፦ ቍጥር 15. ጥበብ መረዳትና የሕግ ዕውቀት ከጌታ ይመጣል፤ በጎ ተግባርና መልካም ሥራ መፈጸም ከእርሱ ይመጣሉ። ቍጥር 16. ስንፍናና ጭለማ ለኃጢአተኞች የተፈጠሩ ነበሩ፤ እነዚህ በክፋት ለሚደሰቱትና በክፋት ላረጁትም ናቸው። 17በእግዚአብሔር ለታመኑ ስጦታው አይነጥፍም፤ እርዳታውም ሁሌ ከእነርሱ ጋር ነው። 18#መዝ. 48፥11፤ ሉቃ. 12፥16-21።ሌሎች በንፍገት ሀብት ያከማቻሉ፤ ታዲያ ዋጋቸው ምን እንደሆነ እነሆ ተመልከቱ፤ 19ሰው “ዕረፍት አግኝቻለሁ፤ አሁን ያለኝን እየበላሁ እኖራለሁ” ሲል ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ አያውቅም፤ ገንዘቡን ለሌሎች ትቶ ይሞታል። 20ሥራህን አጥብቀህ ያዝ በርትተህም ሥራ፤ በሥራህም ጸንተህ አርጅ። 21በኃጢአተኛ ሥራ አትደነቅ፤ በእግዚአብሔር ተማመን፤ በሥራህ ጸንተህ ኑር፤ በድንገት ባንድ አፍታ ድኃውን ማበልጸግ ለእግዚአብሔር ቀላል ነውና። 22የጻድቅ ሰው ዋጋው የእግዚአብሔር ቡራኬ ነው፤ እግዚአብሔር ባንድ ጊዜ ቡራኬውን እንዲያብብ ያደርገዋል። 23“ምን የሚቸግረኝ ነገር አለ? ለወደፊት ምን ያህል ገንዘብ ያስፈልገኛል?” አትበል። 24“የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ አለኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምን መከራ ይመጣብኛል?” አትበል። 25በደስታ ቀን ክፉ ነገር ይረሳል፤ በመከራ ቀን ደስታ አይታወስም። 26በሞት ጊዜ ለያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው ዋጋውን መክፈል ለእግዚአብሔር ቀላል ነው። 27ቅጽበታዊ መከራና ደስታ ይረሳሉ፤ በሰው የሕይወቱ የመጨረሻ ሰዓት የሠራው ሁሉ ይገለጣል። 28ሰውን ከመሞቱ በፊት የታደለ ነው አትበለው፤ እርሱን የምታውቀው ሲሞት ነውና።
ክፉን ሰው አትመን
29ሁሉንም ሰው ወደ ቤትህ አታምጣ፤ አብዛኞቹ የተንኮለኞች ወጥመድ ናቸውና። 30የትዕቢተኛ ልብ በጐጆዋ ውስጥ በወጥመድ እንደ ተያዘች ቆቅ ነው፤ እንደ ሰላይ ውድቀትህን ይጠባበቃል። 31ሁሌም ስለሚከታተልህ ደጉን ወደ ክፉ ይለውጣል፤ ድንቅ የሚሰኝለትንም ሥራ አቃቅር ያወጣለታል። 32ምድጃ ሙሉ ፍም ከሰል የሚቀጣጠለው፥ ከአንድ ብልጭታ ነው፤ ኃጢአተኛው ደም ለማፍሰስ ተዘጋጅቶ ይጠባበቃል። 33ከክፉ ሰው እና ከሴራዎቹ ተጠበቅ፤ ለዘለዓለም ሊያጠቃህ ይችላልና። 34ባዕድ ሰው ብታስጠጋ ችግር ይፈጥርብሃል፤ ከቤተሰብህም ያለያይሃል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 11: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ