የዮሐንስ ራእይ 3:7-22

የዮሐንስ ራእይ 3:7-22 መቅካእኤ

“በፊላደልፊያም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ ‘ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፥ የዳዊትም መክፈቻ ያለው፥ ሲከፍትም፥ ማንም የማይዘጋው፤ ሲዘጋም ማንም የማይከፍተው፤ እርሱ እንዲህ ይላል’፦ “ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፤ ማንም ሊዘጋውም አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፤ ስሜንም አልካድህምና። እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ ‘አይሁድ ነን’ ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ለመፈተን በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ። እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ። ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዓምድ አደርገዋለሁ፤ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለትም ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌምን ስም፥ እንዲሁም አዲሱን ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። “በሎዲቅያም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ የእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦ “ሥራህን አውቃለሁ፥ በራድ ወይም ትኩስ አለመሆንህን። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆን ኖሮ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። ‘ሀብታም ነኝና ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ፤ አንድም ነገር አያስፈልገኝም፤’ የምትል ስለ ሆንክ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዐይነ ስውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥ ሀብታም እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ የምትጐናጸፈውን ነጭ ልብስ፥ እንድታይም ዐይኖችህን የምትኳልበትን ኩል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ። እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ተነሣሣ፤ ንስሓም ግባ። እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። እኔም ድል እንደ ነሣሁ፥ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።”