ራእይ 3:7-22

ራእይ 3:7-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“በፊላደልፊያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፡ የዳዊት መክፈቻ ያለው፥ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ፥ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል፦ “ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፤ ማንም ሊዘጋውም አይችልም፤ ኀይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፤ ስሜንም አልካድህምና። እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ ‘አይሁድ ነን’ ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ። እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ። ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፤ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። “በሎዲቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፡ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦ “በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። ‘ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ፤ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም፤’ የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥ ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዐይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ። እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና፤ ንስሓም ግባ። እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።”

ራእይ 3:7-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“በፊላድልፍያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፣ የዳዊትንም መክፈቻ በእጁ የያዘው እንዲህ ይላል፤ እርሱ የከፈተውን ማንም ሊዘጋው አይችልም፤ የዘጋውንም ማንም ሊከፍተው አይችልም። ሥራህን ዐውቃለሁ። እነሆ፤ ማንም ሊዘጋው የማይችል የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌአለሁ። ኀይልህ ትንሽ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ ሆኖም ቃሌን ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድህም። እነሆ፣ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉት፣ የሚዋሹት፣ የሰይጣን ማኅበር የሆኑት ወደ አንተ እንዲመጡ በእግርህ ሥር እንዲሰግዱ፣ እኔ እንደ ወደድሁህም እንዲያውቁ አደርጋለሁ። በትዕግሥት እንድትጸና የሰጠሁህን ትእዛዜን ስለ ጠበቅህ፣ እኔ ደግሞ በምድር ላይ የሚኖሩትን ሊፈትናቸው በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ። ቶሎ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጥብቀህ ያዝ። ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ውስጥ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም። የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም ይኸውም ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም ስም በርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ አዲሱን ስሜንም በርሱ ላይ እጽፋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። “በሎዶቅያ ላለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ አሜን የሆነው፣ ደግሞም ታማኝና እውነተኛ ምስክር የሆነው፣ የእግዚአብሔርም ፍጥረት ምንጭ የሆነው እንዲህ ይላል። ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ እንዳልሆንህ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኵስ ብትሆን በወደድሁ ነበር። እንግዲህ ለብ ያልህ ብቻ እንጂ ትኵስ ወይም ቀዝቃዛ ስላልሆንህ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው። ‘ሀብታም ነኝ፣ ባለጠጋ ነኝ፣ አንዳችም አያስፈልገኝም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፣ ምስኪን፣ ድኻ፣ ዕውርና የተራቈትህ መሆንህን አታውቅም። ስለዚህ ሀብታም እንድትሆን፣ በእሳት የነጠረ ወርቅ እንድትገዛ፣ የዕራቍትነትህ ኀፍረት እንዳይታይ፣ ነጭ ልብስ እንድትለብስና ለማየት እንድትችል ዐይንህን በኵል እንድትኳል እመክርሃለሁ። እኔ የምወድዳቸውን እገሥጻለሁ፤ እቀጣለሁም። ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ። እነሆ፤ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከርሱ ጋራ እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋራ ይበላል። እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋራ በርሱ ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋራ በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።”

ራእይ 3:7-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በፊልድልፍያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ፥ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል፦ ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፥ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፥ ስሜንም አልካድህምና። እነሆ፥ አይሁድ ሳይሆኑ፦ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፥ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ። እነሆ፥ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ። ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦ በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥ ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ። እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ገባ። እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።

ራእይ 3:7-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“ለፊላደልፍያ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ “ይህ፥ ቅዱስና እውነተኛ ከሆነው፥ የዳዊት ቤት ቊልፍ ከያዘው የተነገረ ነው፤ እርሱ የሚከፍተውን ማንም አይዘጋውም፤ እርሱ የሚዘጋውንም ማንም አይከፍተውም። ሥራህን ዐውቃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም ሊዘጋው የማይችለውን የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌልሃለሁ፤ ኀይልህ ትንሽ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ቃሌን ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድክም። እንግዲህ፥ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉትን እነዚያን ከሰይጣን ማኅበር የሆኑትን ውሸታሞች መጥተው በእግርህ ሥር እንዲወድቁ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኩህም እንዲያውቁ አደርጋቸዋለሁ። ትዕግሥተኛ ሁን ያልኩህን ቃሌን ስለ ጠበቅህ እኔም በምድር ላይ የሚኖሩትን ሊፈትናቸው በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው ከመከራ ሰዓት እጠብቅሃለሁ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፤ አክሊልህን ማንም እንዳይወስድብህ ያለህን አጥብቀህ ያዝ። ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ ይህችም ከተማ ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ናት፤ የእኔንም አዲስ ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ! “ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ “ይህ፥ አሜን ከሆነው፥ ታማኝና እውነተኛ ምስክር ከሆነው፥ የእግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ መገኛ ከሆነው የተነገረ ነው፤ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ አይደለህም፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ ብትሆን ኖሮ መልካም በሆነ ነበር! ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ ሳትሆን ለብ ያልክ ስለ ሆንክ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው፤ ‘እኔ ሀብታም ነኝ፤ ብዙ ሀብት አለኝ፤ የሚጐድለኝ ምንም የለም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፥ ምስኪን፥ ድኻ፥ ዕውርና የተራቈትህ መሆንክን አታውቅም፤ ሀብታም ለመሆን በእሳት የተፈተነውን ወርቅ ከእኔ እንድትገዛ፥ የራቊትነትህን ኀፍረት ለመሸፈን ነጭ ልብስ እንድትለብስ፥ ለማየትም እንድችል የዐይን መድኃኒት ገዝተህ እንድትቀባ እመክርሃለሁ። እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸዋለሁም፤ ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ፤ እነሆ! እኔ በበር ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል፤ እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋር በዙፋኑ ላይ እንደ ተቀመጥኩ እንዲሁም ድል የነሣ ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ። “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!”

ራእይ 3:7-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“በፊላደልፊያም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ ‘ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፥ የዳዊትም መክፈቻ ያለው፥ ሲከፍትም፥ ማንም የማይዘጋው፤ ሲዘጋም ማንም የማይከፍተው፤ እርሱ እንዲህ ይላል’፦ “ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፤ ማንም ሊዘጋውም አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፤ ስሜንም አልካድህምና። እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ ‘አይሁድ ነን’ ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ለመፈተን በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ። እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ። ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዓምድ አደርገዋለሁ፤ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለትም ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌምን ስም፥ እንዲሁም አዲሱን ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። “በሎዲቅያም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ የእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦ “ሥራህን አውቃለሁ፥ በራድ ወይም ትኩስ አለመሆንህን። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆን ኖሮ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። ‘ሀብታም ነኝና ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ፤ አንድም ነገር አያስፈልገኝም፤’ የምትል ስለ ሆንክ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዐይነ ስውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥ ሀብታም እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ የምትጐናጸፈውን ነጭ ልብስ፥ እንድታይም ዐይኖችህን የምትኳልበትን ኩል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ። እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ተነሣሣ፤ ንስሓም ግባ። እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። እኔም ድል እንደ ነሣሁ፥ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።”