የዮሐንስ ራእይ 3:7-22

የዮሐንስ ራእይ 3:7-22 አማ05

“ለፊላደልፍያ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ “ይህ፥ ቅዱስና እውነተኛ ከሆነው፥ የዳዊት ቤት ቊልፍ ከያዘው የተነገረ ነው፤ እርሱ የሚከፍተውን ማንም አይዘጋውም፤ እርሱ የሚዘጋውንም ማንም አይከፍተውም። ሥራህን ዐውቃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም ሊዘጋው የማይችለውን የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌልሃለሁ፤ ኀይልህ ትንሽ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ቃሌን ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድክም። እንግዲህ፥ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉትን እነዚያን ከሰይጣን ማኅበር የሆኑትን ውሸታሞች መጥተው በእግርህ ሥር እንዲወድቁ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኩህም እንዲያውቁ አደርጋቸዋለሁ። ትዕግሥተኛ ሁን ያልኩህን ቃሌን ስለ ጠበቅህ እኔም በምድር ላይ የሚኖሩትን ሊፈትናቸው በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው ከመከራ ሰዓት እጠብቅሃለሁ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፤ አክሊልህን ማንም እንዳይወስድብህ ያለህን አጥብቀህ ያዝ። ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ ይህችም ከተማ ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ናት፤ የእኔንም አዲስ ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ! “ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ “ይህ፥ አሜን ከሆነው፥ ታማኝና እውነተኛ ምስክር ከሆነው፥ የእግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ መገኛ ከሆነው የተነገረ ነው፤ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ አይደለህም፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ ብትሆን ኖሮ መልካም በሆነ ነበር! ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ ሳትሆን ለብ ያልክ ስለ ሆንክ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው፤ ‘እኔ ሀብታም ነኝ፤ ብዙ ሀብት አለኝ፤ የሚጐድለኝ ምንም የለም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፥ ምስኪን፥ ድኻ፥ ዕውርና የተራቈትህ መሆንክን አታውቅም፤ ሀብታም ለመሆን በእሳት የተፈተነውን ወርቅ ከእኔ እንድትገዛ፥ የራቊትነትህን ኀፍረት ለመሸፈን ነጭ ልብስ እንድትለብስ፥ ለማየትም እንድችል የዐይን መድኃኒት ገዝተህ እንድትቀባ እመክርሃለሁ። እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸዋለሁም፤ ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ፤ እነሆ! እኔ በበር ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል፤ እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋር በዙፋኑ ላይ እንደ ተቀመጥኩ እንዲሁም ድል የነሣ ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ። “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!”