የማቴዎስ ወንጌል 8:1-12

የማቴዎስ ወንጌል 8:1-12 መቅካእኤ

ከተራራው በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆ አንድ ለምጻም መጥቶ ሰገደለትና “ጌታ ሆይ! ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ” አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ። ኢየሱስም “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ” አለው። ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ በመለመን፥ “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሠቃየ በቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃውም እንዲህ ሲል መለሰ “ጌታ ሆይ! ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ራሴ ከባለሥልጣኖች በታች ነኝ፤ ከእኔ በታች ደግሞ ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን ደግሞ ‘ና’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ይከተሉት የነበሩትን እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋርም በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥቱ ልጆች ግን ውጪ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች