ማቴዎስ 8:1-12

ማቴዎስ 8:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆም፥ ለምጻም ቀርቦ “ጌታ ሆይ! ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” እያለ ሰገደለት። እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና “እወዳለሁ፤ ንጻ” አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ። ኢየሱስም “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ” አለው። ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ “ጌታ ሆይ!ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል” ብሎ ለመነው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃውም መልሶ “ጌታ ሆይ! በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፤ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም ‘ሂድ’ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና’ ብለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም ‘ይህን አድርግ’ ብለው ያደርጋል” አለው። ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ “እውነት እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

ማቴዎስ 8:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከተራራው በወረደ ጊዜም ብዙ ሕዝብ ተከተለው። እነሆ፤ አንድ ለምጻም ሰው ወደ ኢየሱስ ቀረበና ከፊቱ ተንበርክኮ እየሰገደለት፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። ከዚያም ኢየሱስ፣ “መፈወስህን ለማንም አታውራ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ፤ ይህም ምስክር ይሆንላቸዋል” አለው። ኢየሱስ ቅፍርናሆም እንደ ደረሰ አንድ የመቶ አለቃ ቀርቦ፣ እንዲህ ሲል ለመነው፤ “ጌታ ሆይ፤ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ በመሠቃየት ከቤት ተኝቷል” አለው። ኢየሱስም፣ “እኔ መጥቼ ልፈውሰውን?” አለው። የመቶ አለቃው ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል፤ እኔ ራሴ የምታዘዛቸው አለቆች፣ ለእኔም የሚታዘዙ የበታቾች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን፣ ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤ እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ከአብርሃም፣ ከይሥሐቅና ከያዕቆብ ጋራ በማእድ ይቀመጣሉ፤ መንግሥተ ሰማይ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ግን ወደ ውጭ ወደ ጨለማው ይጣላሉ። በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

ማቴዎስ 8:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆም፥ ለምጻም ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ እያለ ሰገደለት። እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና፦ እወዳለሁ፥ ንጻ አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ። ኢየሱስም፦ ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ አለው። ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል ብሎ ለመነው። ኢየሱስም፦ እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ አለው። የመቶ አለቃውም መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ ከታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም፦ ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም፦ ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም፦ ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል አለው። ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

ማቴዎስ 8:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ከተራራው በወረደ ጊዜ፥ እጅግ ብዙ ሰዎች ተከተሉት። በዚህ ጊዜ አንድ ለምጻም ሰው መጥቶ ሰገደለትና “ጌታ ሆይ! ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለ። ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “ፈቅጃለሁ፤ ንጻ!” አለው። ለምጻሙም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፥ ከለምጹ የዳነውን ሰው እንዲህ አለው፤ “ይህን ነገር ለማንም አትናገር፤ ነገር ግን ሄደህ መዳንህን ለካህን አሳይ፤ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ፥ ስለ መዳንህ ሙሴ ያዘዘውን መባ ለእግዚአብሔር አቅርብ” አለው። ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም ከተማ በገባ ጊዜ፥ አንድ ሮማዊ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ በመለመን፥ “ጌታ ሆይ፥ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ፥ እጅግ በመሠቃየት በቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃው ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ቤቴ እንድትገባ እኔ የተገባሁ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይድናል። እኔ ራሴ ለባለ ሥልጣኖች ታዛዥ ስሆን፥ ከእኔ በታች የማዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ ተደነቀ፤ ይከተሉት የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህን የሚያኽል ትልቅ እምነት ያለው አንድም ሰው በእስራኤል ስንኳ አላገኘሁም። ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፥ ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብ ጋር በመንግሥተ ሰማይ በማዕድ ይቀመጣሉ እላችኋለሁ። የዚህ መንግሥት ወራሾች መሆን ይገባቸው የነበሩት ግን ውጪ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ። በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

ማቴዎስ 8:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከተራራው በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆ አንድ ለምጻም መጥቶ ሰገደለትና “ጌታ ሆይ! ብትፈቅድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ” አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ። ኢየሱስም “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ” አለው። ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ በመለመን፥ “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሠቃየ በቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃውም እንዲህ ሲል መለሰ “ጌታ ሆይ! ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ራሴ ከባለሥልጣኖች በታች ነኝ፤ ከእኔ በታች ደግሞ ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን ደግሞ ‘ና’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ይከተሉት የነበሩትን እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋርም በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥቱ ልጆች ግን ውጪ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”