ማቴዎስ 8:1-12

ማቴዎስ 8:1-12 NASV

ከተራራው በወረደ ጊዜም ብዙ ሕዝብ ተከተለው። እነሆ፤ አንድ ለምጻም ሰው ወደ ኢየሱስ ቀረበና ከፊቱ ተንበርክኮ እየሰገደለት፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ከለምጹ ነጻ። ከዚያም ኢየሱስ፣ “መፈወስህን ለማንም አታውራ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ፤ ይህም ምስክር ይሆንላቸዋል” አለው። ኢየሱስ ቅፍርናሆም እንደ ደረሰ አንድ የመቶ አለቃ ቀርቦ፣ እንዲህ ሲል ለመነው፤ “ጌታ ሆይ፤ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ በመሠቃየት ከቤት ተኝቷል” አለው። ኢየሱስም፣ “እኔ መጥቼ ልፈውሰውን?” አለው። የመቶ አለቃው ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል፤ እኔ ራሴ የምታዘዛቸው አለቆች፣ ለእኔም የሚታዘዙ የበታቾች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን፣ ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤ እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ከአብርሃም፣ ከይሥሐቅና ከያዕቆብ ጋራ በማእድ ይቀመጣሉ፤ መንግሥተ ሰማይ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ግን ወደ ውጭ ወደ ጨለማው ይጣላሉ። በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች