የሉቃስ ወንጌል 8:3-12

የሉቃስ ወንጌል 8:3-12 መቅካእኤ

የሄሮድስ መጋቢ የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናና ብዙዎች ሌሎችም ሆነው ከንብረታቸው በመጠቀም ያገለግሉአቸው ነበር። ብዙ ሕዝብም በተሰበሰበና ከየከተማውም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ እንዲህ ሲል በምሳሌ ተናገረ፦ “ዘሪ ዘሩን ለመዝራት ወጣ። በሚዘራበትም ጊዜ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ተረገጠም፤ የሰማይ ወፎችም ጨረሱት። ሌላውም በዐለት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህንንም እየተናገረ፦ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፤” ብሎ ጮኸ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “ይህ ምሳሌ ትርጓሜው ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌዎች ይነገራቸዋል” አላቸው። “የምሳሌውም ትርጒም ይህ ነው፦ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሰሙት ናቸው፤ ከዚያ በኋላም አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።