የሉቃስ ወንጌል 8:3-12
የሉቃስ ወንጌል 8:3-12 አማ05
የሄሮድስ ቤት አዛዥ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናና ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህ ሴቶች ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን በገንዘባቸው ያገለግሉ ነበር። ብዙ ሕዝብ ከየከተማው ወደ እርሱ መጥተው በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ተረገጠ፤ ወፎችም በሉት። ሌላውም ዘር በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መሬቱ እርጥበት ስላልነበረው ቡቃያው ደረቀ። ሌላውም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹ አብሮ አደገና አንቆ አስቀረው። ሌላው ዘር ግን በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለ፤ ቡቃያውም አድጎ እያንዳንዱ መቶ እጥፍ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” አለ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “የዚህ ምሳሌ ትርጒም ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ሌሎች ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ እነርሱ እያዩ ልብ እንዳያደርጉ፥ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።” የምሳሌው ትርጒም ይህ ነው፦ “ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።

