ሉቃስ 8:3-12
ሉቃስ 8:3-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሄሮድስ አዛዥ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናም፥ በገንዘባቸው ያገለግሉት የነበሩ ብዙዎች ሌሎችም ነበሩ። ሕዝቡም ሁሉ፥ ከየከተማዉም ሁሉ ወደ እርሱ የመጡት ሲያዳምጡት እንዲህ ያለ ምሳሌ ነገራቸው። “ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ወደቀና ተረገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት። ሌላውም በጭንጫ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ ወዲያው ደረቀ፤ ሥር አልነበረውምና። ሌላዉም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾሁም አብሮ አደገና አነቀው። በመልካም መሬት ላይ የወደቀ ዘርም ነበረ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህንም ብሎ፥ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፥ “ይህቺ ምሳሌ ምንድን ናት?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነዚያ ግን አይተው እንዳያዩ፥ ሰምተውም እንዳይሰሙ፥ እንዳያስተውሉም በምሳሌ ነው። ምሳሌዉም ይህ ነው፤ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንገድ የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ ናቸው፤ አምነውም እንዳይድኑ ሰይጣን መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስድባቸዋል።
ሉቃስ 8:3-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የሄሮድስ ቤት ኀላፊ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና፣ ደግሞም ሌሎች ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህም በግል ንብረታቸው የሚያገለግሉት ነበሩ። ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስቦ ሳለ፣ ደግሞም ሰዎች ከተለያዩ ከተሞች ወደ እርሱ በሚጐርፉበት ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ዐራሽ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፣ በእግርም ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት። አንዳንዱም ዘር በድንጋያማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ እንደ በቀለም ርጥበት አልነበረውምና ደረቀ። ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም ዐብሮት አደገና ዐንቆ አስቀረው። ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ ዕጥፍ አፈራ።” ይህን ብሎ ሲያበቃም ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ። ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጕም ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቷል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣ “ ‘እያዩ ልብ እንዳይሉ፣ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።’ “እንግዲህ የምሳሌው ትርጕም ይህ ነው፤ ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳር የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ፣ ነገር ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው።
ሉቃስ 8:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የሄሮድስ አዛዥ የኩዛ ሚስት ዮሐናም ሶስናም ብዙዎች ሌሎችም ሆነው በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር። ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ ከከተማዎችም ሁሉ ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በምሳሌ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ ተረገጠም፥ የሰማይ ወፎችም በሉት። ሌላውም በዓለት ላይ ወደቀ፥ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ። ይህን በተናገረ ጊዜ፦ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ብሎ ጮኸ። ደቀ መዛሙርቱም፦ ይህ ምሳሌ ምንድር ነው? ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አለ፦ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌ ነው። ምሳሌው ይህ ነው። ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።
ሉቃስ 8:3-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የሄሮድስ ቤት አዛዥ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናና ሌሎችም ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህ ሴቶች ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን በገንዘባቸው ያገለግሉ ነበር። ብዙ ሕዝብ ከየከተማው ወደ እርሱ መጥተው በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ተረገጠ፤ ወፎችም በሉት። ሌላውም ዘር በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መሬቱ እርጥበት ስላልነበረው ቡቃያው ደረቀ። ሌላውም ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹ አብሮ አደገና አንቆ አስቀረው። ሌላው ዘር ግን በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለ፤ ቡቃያውም አድጎ እያንዳንዱ መቶ እጥፍ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” አለ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን “የዚህ ምሳሌ ትርጒም ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ሌሎች ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ እነርሱ እያዩ ልብ እንዳያደርጉ፥ እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።” የምሳሌው ትርጒም ይህ ነው፦ “ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን ለጊዜው የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ ነገር ግን እነርሱ አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።
ሉቃስ 8:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሄሮድስ መጋቢ የኩዛ ሚስት ዮሐና፥ ሶስናና ብዙዎች ሌሎችም ሆነው ከንብረታቸው በመጠቀም ያገለግሉአቸው ነበር። ብዙ ሕዝብም በተሰበሰበና ከየከተማውም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ እንዲህ ሲል በምሳሌ ተናገረ፦ “ዘሪ ዘሩን ለመዝራት ወጣ። በሚዘራበትም ጊዜ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ተረገጠም፤ የሰማይ ወፎችም ጨረሱት። ሌላውም በዐለት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ እጥፍ አፈራ።” ይህንንም እየተናገረ፦ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፤” ብሎ ጮኸ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “ይህ ምሳሌ ትርጓሜው ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለሌሎች ግን እያዩ እንዳያዩ እየሰሙም እንዳያስተውሉ በምሳሌዎች ይነገራቸዋል” አላቸው። “የምሳሌውም ትርጒም ይህ ነው፦ ዘሩ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በመንገድ ዳርም ያሉት የሰሙት ናቸው፤ ከዚያ በኋላም አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።