የዮሐንስ ወንጌል 21:4-14

የዮሐንስ ወንጌል 21:4-14 መቅካእኤ

በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀመዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። “የለንም” ብለው መለሱለት። እርሱም “መረቡን በታንኳዪቱ በስተ ቀኝ ጣሉትና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህም ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጎተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀመዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ እኮ ነው” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ዘለለ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። ወደ የብስ በወጡ ጊዜ ዓሣ በላዩ የተቀመጠበት ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንንም ያህል ብዙ ዓሣ ይዞ መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ብሉ” አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ እንኳን “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና። ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፤ እንዲሁም ዓሣውን። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ።