መጽሐፈ ዮዲት 15
15
1በየድንኳኖቹ የነበሩ ሰዎች የሆነውን ነገር በሰሙ ጊዜ በጣም ደነገጡ፤ 2መንቀጥቀጥና ፍርሃት ወደቀባቸው፥ ከባልንጀራው ጋር የቆየ አልነበረም፥ ሁሉም በሜዳውና በተራራማው አገር በአገኙት መንገድ በአንድነት ሸሹ። 3በቤቱሊያ አካባቢ ባለው በተራራማው አገር ሰፍረው የነበሩት ሸሹ። በዚህ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ወታደር የሆኑ ሁሉ ፈጥነው ተከተሏቸው። 4ዑዚያም የሆነውን ነገር እንዲናገሩና ጠላቶቻቸውን ተከታትለው እንዲያጠፏቸው ወደ ቤቶማስታይም፥ ወደ ቤባይ፥ ወደ ቾባ፥ ወደ ኮላና ወደ እስራኤል አውራጃ ሁሉ ላከ። 5የእስራኤልም ልጆች ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም በአንድነት አጠቁአቸው እስከ ቾባ ድረስ እየተከተሉ ገደሉአቸው፤ በጠላቶቻቸው ሰፈር የደረሰው ነገር ተነግሮአቸዋልና በኢየሩሳሌምና በተራራ አገር የሚኖሩ ሁሉ መጡ፤ የገለዓድና የገሊላ ሰዎችም ከደማስቆና ከድንበርዋ ባሻገር በታላቅ እልቂት አጠፏቸው። 6የቀሩት የቤቱሊያ ነዋሪዎች ወደ አሦራውያን ጦር ሰፈር ገብተው ዘረፉ፥ ብዙ ሀብትም አገኙ። 7ከዚህ በኋላ የእስራኤል ልጆች ከጦርነቱ ሲመለሱ የተረፈውን ዘረፉ፥ ብዙ ነበርና የተራራማውና የሜዳው አገር ከተሞችና ገጠሮች ብዙ ምርኮ አገኙ።
ምስጋና
8ሊቀ ካህኑ ኢዮአቄምና በኢየሩሳሌም የሚቀመጡ የእስራኤል ሽማግሌዎች ጉባኤ፥ ጌታ ለእስራኤል የደረገውን መልካም ሥራ ለማየት፥ ዮዲትንም ለማየትና ለእርሷም ሰላምታ ለማቅረብ መጡ። 9ወደ እርሷም በገቡ ጊዜ ሁሉም በአንድነት እንዲህ ሲሉ መረቋት፦ “አንቺ የኢየሩሳሌም ክብር ነሽ፥ የእስራኤል ታላቅ መመኪያና የዘራችንም ታላቅ ኩራት ነሽ፥ 10ይህን ሁሉ በእጅሽ አደረግሽ፤ ለእስራኤልም ብዙ መልካም ነገር አደረግሽ፥ እግዚአብሔርም በዚህ ተደስቷል፤ ሁሉን የሚችል ጌታ ለዘለዓለም ይባርክሽ!” ሕዝቡም ሁሉ “አሜን” አሉ። 11ሕዝቡም ሁሉ የጦር ሰፈሩን ሠላሳ ቀን ያህል ዘረፉ፥ ለዮዲትም የሆሎፎርኒስን ድንኳንና የብሩን ሣህን ሁሉ፥ አልጋዎቹንና ጎድጓዳ ሣህኖቹን፥ የቤት ዕቃዎቹን ሁሉ ሰጧት፤ እርሷም ወስዳ በበቅሎዋ ላይ ጫነች፤ ሠረገላዎችዋንም አዘጋጀትና እዚያ ላይ ጫነችው። 12የእስራኤል ሴቶች ሁሉ እርሷን ለማየት ወደ እርሷ ተሰብስቡ፥ መረቋትም፤ ለእርሷም ክብር ዘፈኑላት፤ በእጆችዋ ቅጠላም ሐረግ በእጇ ይዛ ከእርሷ ጋር ለነበሩ ሴቶችም ሰጠቻቸው። 13እርሷና ከእርሷ ጋር የነበሩ ሴቶች የወይራ ቅጠል አክሊል በራሳቸው ላይ አደረጉ፤ እርሷ ሴቶቹን ሁሉ በዘፈን እየመራች ከሕዝቡ ሁሉ ፊት ሄደች፤ የእስራኤልም ወንዶች ሁሉ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው፥ አክሊል በራሳቸው ላይ ደፍተው በአፋቸው እየዘመሩ ተከተሏት። 14ዮዲትም ይህን የምስጋና መዝሙር በመላው እስራኤል ሕዝብ መካከል ጀመረች፥ ሕዝቡም ሁሉ ይህንን የምስጋና መዝሙር ጮክ ብሎ ዘመረ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዮዲት 15: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ