መጽሐፈ ዮዲት 16

16
1ዮዲት እንዲህ አለች፤ “ለአምላኬ በከበሮ መዝሙርን ጀምሩ፥ ለጌታ በጸናጽን ዘምሩለት፤ አዲስን መዝሙር ተቀኙለት፤ አክብሩት፥ ስሙንም ጥሩ። 2ጌታ ሰልፍን የሚሰብር አምላክ ነውና፤ የጦር ሰፈሩን በሕዝቡ መካከል አደረገ፤ ከሚያሳድዱኝም ሰዎች እጅ አዳነኝ። 3አሦር ከሰሜን ተራራዎች ወጣ፤ ከብዙ ሺህ ሠራዊቱም ጋር ወጣ። ብዛታቸው ፈሳሹን ዘጋ፤ ፈረሶቻቸው ኮረብታዎችን ሸፈነ። 4ድንበሬን ሊያቃጥል፥ ጐልማሶቼን በሰይፍ ሊገድል፥ ጨቅላ ልጆቼን በምድር ላይ ሊጥል፥ ሕጻናቴንና ደናግላኔንም በምርኮ ሊወስድ ደፍሮ ተናግሮ ነበር። 5ነገር ግን ሁሉን የሚችል ጌታ ሴት እጅ አስቆማቸው። 6ኃያላቸው በጐልማሶች እጅ አልወደቀም፤ የቲታንስ ልጆችም አልመቱትም፤ ረጃጅም ግዙፎችም አላጠቁትም፤ የሜራሪ ልጅ ዮዲት ግን በውበቷ ሽባ አደረገችው። 7በእስራኤል የተጨቆኑትን ለማንሳት የመበለትነቷን ልብስ አወለቀች፥ ፊትዋንም ቅባት ተቀባች። 8ጠጉርዋን ተሠርታ ሻሽ አሰረች፤ ለመሳብም የተልባ እግር ልብስ ለበሰች። 9ጫማዋ ዐይኖቹን ያዘ፤ ውበቷ ነፍሱን ማረከ፤ ሰይፉም በአንገቱ አለፈ። 10የፋርስ ሰዎች በድፍረቷ ደነገጡ፤ የሜዶን ሰዎች በጽናቷ ፈሩ። 11በዚያን ጊዜ የእኔ ትሑታን ጮኹ፥ የእኔ ደካሞች በጣም ጮኹ፤ እነዚያም በድንጋጤ ተዋጡ፤ የእኔ ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አደረጉ፥ እነዚያም ደንግጠው ሸሹ። 12የሴቶች ልጆች#16፥12 የገረዶች ልጆች። ወጉአቸው፤ እንደ ከሐዲ ልጆችም አቆሰሏቸው፤ በጌታዬ ሰልፍም ጠፉ። 13#መዝ. 143፥9።ለአምላኬ አዲስ የምስጋናን መዝሙር እዘምራለሁ፤ ጌታ ሆይ አንተ ትልቅና ክቡር፥ በብርታትህ የምትደነቅና የማትሸንፍ ነህ። 14ፍጥረቶችህ ሁሉ ያገልግሉህ፤ አንተ ተናገርህ እነርሱም ተፈጠሩ፤ መንፈስህን ላክህ፥ እነርሱም ታነጹ፤ ድምጽህን መቃወም የሚችል ማንም የለም። 15ተራሮች ከውኆች ጋር ከመሠረታቸው ይንዋወጣሉና፤ ዓለቶችም በአንተ ፊት እንደ ሰም ይቀልጣሉ፤ ለሚፈሩህ ግን ምሕረትን ታደርጋለህ። 16#1ሳሙ. 15፥22፤ መዝ. 50፥18፤19፤ ሆሴዕ 6፥6።ጥሩ መዓዛ ያለው መሥዋዕት ሁሉ ለአንተ ትንሽ ነው፥ የሚቃጠለው መሥዋዕት ሁሉ ስብ ለአንተ በጣም ጥቂት ነው፤ ጌታን የሚፈራ ግን ሁልጊዜ ታላቅ ነው። 17በወገኖቼ ላይ የሚነሡ አሕዛብ ወዮላቸው፤ ሁሉን የሚችል ጌታ በፍርድ ቀን ይበቀላቸዋል፤ በሥጋቸውም ላይ እሳትንና ትልን ያመጣባቸዋል፤ በስቃይም ለዘለዓለም ያለቅሳሉ።” 18ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ ሕዝቡም በነጹ ጊዜ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና በፈቃዳቸው የሚያቀርቡት መባዎችንና ስጦታዎችን አቀረቡ። 19ዮዲትም ሕዝቡ የሰጣትን የሆሎፎርኒስን ንብረቶች ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረበች። ከመኝታ ቤቱ ያመጣችውን መጋረጃ እንደ ስእለት አድርጋ ለጌታ ሰጠች። 20ሕዝቡ ሁሉ በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደስ ፊት ሦስት ወር ሙሉ ደስታ አደረጉ፤ ዮዲትም ከእነርሱ ጋር ተቀመጠች።
የዮዲት እርጅናና እረፍት
21ከዚህ ጊዜ በኋላ እያንዳንዱ ወደ ርስቱ ተመለሰ። ዮዲትም ወደ ቤቱሊያ ተመለሰች፥ በንብረቷም ላይ ተቀመጠች በዘመኗ ሁሉ በምድር ሁሉ ላይ የተከበረች ሆነች። 22ብዙ ሰዎች ሊያገቧት ፈልገው ነበረ፥ ነገር ግን ባሏ ምናሴ ከሞተበትና ወደ ሕዝቡ ከተሰበሰበበት ጊዜ ጀምሮ በሕይወት ዘመኗ ሁሉ ራሷን ለማንም አልሰጠችም። 23እጅግ በጣም ከበረች፥ መቶ አምስት ዓመት እስኪሆናት ድረስ በባሏ ቤት አረጀች፤ አገልጋይዋን ነጻ ለቀቀቻት። በቤቱሊያ ዓረፈች፥ በባሏ በምናሴ ዋሻ ተቀበረች፤ 24የእስራኤል ቤት ለሰባት ቀን አለቀሰላት። ከመሞቷ በፊት ያላትን ሁሉ ለባሏ ለምናሴ የቅርብ ዘመዶችና ለቅርብ ዘመዶቿ አካፈለች። 25ዮዲት በነበረችበት ጊዜና ከሞተችም በኋላ ለብዙ ጊዜ የእስራኤልን ልጆች የሚያስፈራ ማንም አልነበረም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ