ትንቢተ ኢሳይያስ 41:10-20

ትንቢተ ኢሳይያስ 41:10-20 መቅካእኤ

እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳሀለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ። እነሆ፥ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ይዋረዳሉም፤ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፥ ይጠፋሉም። የሚጣሉህንም ትፈልጋቸዋለህ አታገኛቸውምም፥ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ። እኔ አምላክህ ጌታ ነኝ፦ “አትፍራ፥ እረዳሃለሁ” ብዬ ቀኝህን የያዝኩ። አንተ ትል ያዕቆብ፥ ታናሽ እስራኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ እረዳሃለሁ፥ ይላል ጌታ፥ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው። እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፤ ተራሮችንም ታሄዳለህ ታደቅቃቸውማለህ፥ ኮረብቶችንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ታበጥራቸዋለህ፥ ንፋስም ይጠርጋቸዋል፥ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ አንተም በጌታ ደስ ይልሃል፥ በእስራኤልም ቅዱስ ትመካለህ። ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ ጌታ እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆዎችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ ማከማቻ፥ የጥማትንም ምድር ለውሃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። በምድረ በዳ፤ ዝግባን፤ ግራርን፤ ባርሰነትንና ወይራን አበቅላለሁ፤ በበረሃ፤ ጥድን፤ አስታንና ሸውሸዌን በአንድነት እተክላለሁ። ስለዚህ የጌታ እጅ ይህን እንዳደረገ፥ የእስራኤል ቅዱስ እንደፈጠረው፥ ሰዎች እንዲያዩና እንዲያውቁ፥ በአንድነት እንዲገነዘቡ፤ እንዲያስተውሉም።