ትንቢተ ኢሳይያስ 41:1-10

ትንቢተ ኢሳይያስ 41:1-10 መቅካእኤ

ደሴቶች ሆይ፥ በፊቴ ዝም በሉ፤ አሕዛብም ኃይላቸውን ያድሱ፤ ይቅረቡም በዚያን ጊዜም ይናገሩ፤ ለፍርድ በአንድነት እንቅረብ። ከምሥራቅ አንዱን ያስነሣ፥ በጽድቅም ወደ እግሩ የጠራው ማን ነው? አሕዛብንም አሳልፎ በፊቱ ሰጠው፥ ነገሥታትንም አስገዛለት፤ ለሰይፉ እንደ ትቢያ ለቀስቱም እንደ ተጠረገ እብቅ አድርጎ ሰጣቸው። አሳደዳቸው፥ እግሮቹም አስቀድመው ባልሄዱባት ሰላማዊ መንገድ አለፈ። ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራው ማን ነው? እኔ ጌታ፥ መጀመሪያም እስከ መጨረሻውም የምኖር፥ እኔ ነኝ። ደሴቶች አይተው ፈሩ፥ የምድርም ዳርቾች ተንቀጠቀጡ፤ ቀረቡም ደረሱም። ሁሉም እያንዳንዱ ባልንጀራውን ይረዳው ነበር፥ ወንድሙንም፦ “አይዞህ” ይለው ነበር። አናጢውም አንጥረኛውን፥ በመዶሻም የሚያሳሳውን በመስፍ ላይ የሚቀጠቅጠውን ያጽናናዋል፥ ስለ ብየዳ ሥራውም፦ “መልካም ነው” ይለዋል፤ እንዳይላቀቅም በችንካር ያጋጥመዋል። አገልጋዬ እስራኤል፥ የመረጥኩህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፥ አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ ከማዕዘንዋም የጠራሁህና፦ “አንተ አገልጋዬ ነህ፥ መርጬሃለሁ፥ አልጥልህም!” ያልሁህ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳሀለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።