ትንቢተ ሆሴዕ 7:8-16

ትንቢተ ሆሴዕ 7:8-16 መቅካእኤ

ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ሆነ። ባዕዳን ጉልበቱን በዘበዙ፥ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም። የእስራኤልም ትዕቢት በራሱ ላይ መስክሮአል፤ ወደ አምላካቸው ወደ ጌታ ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም። ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌለው እንደ ሞኝ ርግብ ነው፤ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ። በመሄድ ላይ ሳሉ መረቤን በላያቸው እዘረጋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፤ በጉባኤያቸው ላይ እንደተላለፈው እገሥጻቸዋለሁ። ከእኔ ሸሽተው ሄደዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐምፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ እታደጋቸው ነበር፥ እነርሱ ግን ሐሰትን ተናገሩብኝ። በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፤ በእኔም ላይ ዓመፁ። ክንዳቸውን ያስተማርሁና ያጸናሁ እኔ ነበርሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን አሴሩብኝ። ከንቱ ወደ ሆነው ነገር ተመለሱ፤ እንደ ረገበ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸው ከክፉ አንደበታቸው የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።