ሆሴዕ 7:8-16

ሆሴዕ 7:8-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኤፍ​ሬም ከሕ​ዝቡ ጋር ተደ​ባ​ለቀ፤ ኤፍ​ሬም እን​ዳ​ል​ተ​ገ​ላ​በጠ ቂጣ ነው። ጠላት ጕል​በ​ቱን በላው፤ እርሱ ግን አላ​ወ​ቀም፤ ሽበ​ትም ወጣ​በት፤ እር​ሱም ገና አላ​ስ​ተ​ዋ​ለም። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ውር​ደ​ቱና ስድቡ በፊቱ ነው፤ ወደ አም​ላ​ካ​ቸው ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን አል​ተ​መ​ለ​ሱም፤ በዚ​ህም ሁሉ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አል​ፈ​ለ​ጉ​ትም። ኤፍ​ሬ​ምም ልብ እን​ደ​ሌ​ላት እንደ ሰነፍ ርግብ ነው፤ ግብ​ፅን ጠሩ፤ ወደ አሦ​ርም ሄዱ። ሲሄ​ዱም አሽ​ክ​ላ​ዬን እዘ​ረ​ጋ​ባ​ቸ​ዋ​ለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎ​ችም አወ​ር​ዳ​ቸ​ዋ​ለሁ፤ መከ​ራ​ቸ​ውን ሲሰሙ እገ​ሥ​ጻ​ቸ​ዋ​ለሁ። ከእኔ ፈቀቅ ብለ​ዋ​ልና ወዮ​ላ​ቸው! እኔ​ንም ስለ በደሉ ደን​ግ​ጠ​ዋል! እኔ ታደ​ግ​ኋ​ቸው፤ እነ​ርሱ ግን በሐ​ሰት ተና​ገ​ሩ​ብኝ። በመ​ኝ​ታ​ቸው ላይ ሆነው ያለ​ቅሱ ነበር እንጂ በል​ባ​ቸው ወደ እኔ አል​ጮ​ኹም፤ ስለ እህ​ልና ስለ ወይን ይገ​ዳ​ደሉ ነበር፤ በእ​ኔም ዘንድ ተገ​ሠጹ፤ እኔም ክን​ዳ​ቸ​ውን አጸ​ናሁ፤ እነ​ርሱ ግን ክፉ ነገ​ርን መከ​ሩ​ብኝ። ወደ ከንቱ ነገር ተመ​ለሱ፤ እንደ ጠማማ ቀስ​ትም ሆኑ፤ አለ​ቆ​ቻ​ቸ​ውም ከም​ላ​ሳ​ቸው ስን​ፍና የተ​ነሣ በሰ​ይፍ ይወ​ድ​ቃሉ፤ ይህም በግ​ብፅ ምድር ውስጥ መሳ​ለ​ቂያ ይሆ​ን​ባ​ቸ​ዋል።

ሆሴዕ 7:8-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋራ ተደባለቀ፤ ኤፍሬም ያልተገላበጠ ቂጣ ነው። እንግዶች ጕልበቱን በዘበዙ፤ እርሱ ግን አላስተዋለም። ጠጕሩም ሽበት አወጣ፤ እርሱ ግን ልብ አላለም። የእስራኤል ትዕቢት በራሱ ላይ መሰከረበት፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን፣ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም፤ እርሱንም አልፈለገም። “ኤፍሬም በቀላሉ እንደምትታለል፣ አእምሮም እንደሌላት ርግብ ነው፤ አንድ ጊዜ ወደ ግብጽ ይጣራል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ አሦር ይዞራል። ሲበርሩ፣ መረቤን በላያቸው እዘረጋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎችም ጐትቼ አወርዳቸዋለሁ። ስለ ክፉ ሥራቸውም፣ በጉባኤ መካከል እቀጣቸዋለሁ። ወዮ ለእነርሱ፤ ከእኔ ርቀው ሄደዋልና! ጥፋት ይምጣባቸው! በእኔ ላይ ዐምፀዋልና። ልታደጋቸው ፈለግሁ፤ እነርሱ ግን በእኔ ላይ ሐሰት ይናገራሉ። ከልባቸው ወደ እኔ አይጮኹም፤ ነገር ግን በዐልጋቸው ላይ ሆነው ያለቅሳሉ። ስለ እህልና ስለ አዲስ የወይን ጠጅ ይሰበሰባሉ፤ ነገር ግን ከእኔ ዘወር ብለዋል። እኔ አሠለጠንኋቸው፤ አጠነከርኋቸውም፤ እነርሱ ግን ዐደሙብኝ። ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፤ ዒላማውን እንደ ሳተ ቀስት ናቸው፤ መሪዎቻቸው ስለ ክፉ ቃላቸው፣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በዚህም ምክንያት በግብጽ ምድር፣ መዘባበቻ ይሆናሉ።”

ሆሴዕ 7:8-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፥ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው። እንግዶች ጕልበቱን በሉት፥ እርሱም አላወቀም፥ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም። የእስራኤልም ትዕቢት በፊቱ መሰከረ፥ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም። ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌላት እንደ ሰነፍ ርግብ ነው፥ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ። ሲሄዱ አሽክላዬን እዘረጋባቸዋለሁ፥ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፥ መከራቸውን ሲሰሙ እገሥጻቸዋለሁ። ከእኔ ፈቀቅ ብለዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐምፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ ልታደጋቸው ወደድሁ፥ እነርሱ ግን በሐሰት ተናገሩብኝ። በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፥ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፥ በእኔም ላይ ዐመፁ። እኔም ክንዳቸውን አስተማርሁና አጸናሁ፥ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን መከሩብኝ። ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፥ እንደ ተንኰለኛ ቀስት ሆኑ፥ አለቆቻቸው ከምላሳቸው ቍጣ የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።

ሆሴዕ 7:8-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ከአሕዛብ ጋር ተደባለቁ፤ በዚህም ምክንያት እነርሱ እንዳልተገለበጠ ቂጣ የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ባዕዳን ጒልበታቸውን በዘበዙት፤ እነርሱ ግን አልተገነዘቡትም፤ ሽበት ጣል ጣል አድርጎባቸዋል፤ እነርሱ ግን አልተገነዘቡትም። የእስራኤል ሕዝብ ትምክሕታቸው በራሳቸው ላይ ይመሰክርባቸዋል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ወደ እኔ ወደ አምላካቸው አልተመለሱም ከቶም አልፈለጉኝም። የእስራኤል ሕዝብ እንደ ርግብ የዋህና አእምሮ የጐደላቸው ሆነዋል፤ ስለዚህም ርዳታ ለማግኘት አንድ ጊዜ ወደ ግብጽ ይጣራሉ፤ አንድ ጊዜም ወደ አሦር ይበራሉ። በሚዘዋወሩበት ቦታ ሁሉ ወጥመዴን ዘርግቼ እንደ ወፍ እይዛቸዋለሁ፤ ስለ ሠሩትም ክፉ ሥራ እቀጣቸዋለሁ። “ከእኔ ርቀው ስለ ሄዱ ወዮላቸው! በእኔም ላይ ስለ ዐመፁ ጥፋት ይምጣባቸው፤ እኔ ልታደጋቸው ፈልጌ ነበር፤ እነርሱ ግን በእኔ ላይ ሐሰት ይናገራሉ። በአልጋቸው ላይ ተጋድመው ይጮኻሉ እንጂ ከልባቸው ወደ እኔ አይጸልዩም፤ እህልና የወይን ጠጅ ለማግኘት ሰውነታቸውን ይተለትላሉ፤ በእኔም ላይ ያምፃሉ። ያሠለጠንኳቸውና ጒልበታቸው አንዲጠነክር ያደረግኹ እኔ ነኝ፤ እነርሱ ግን በእኔ ላይ ያሤራሉ፤ ከእኔ ርቀው ወደ ከንቱ አምልኮ ተመለሱ፤ ዓላማውን እንደሚስት እንደ ተበላሸ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸውም ክፉ ነገርን ከመናገራቸው የተነሣ በሰይፍ ተመተው ይሞታሉ፤ በግብጻውያንም ዘንድ መዘባበቻ ይሆናሉ።”

ሆሴዕ 7:8-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ሆነ። ባዕዳን ጉልበቱን በዘበዙ፥ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም። የእስራኤልም ትዕቢት በራሱ ላይ መስክሮአል፤ ወደ አምላካቸው ወደ ጌታ ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም። ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌለው እንደ ሞኝ ርግብ ነው፤ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ። በመሄድ ላይ ሳሉ መረቤን በላያቸው እዘረጋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፤ በጉባኤያቸው ላይ እንደተላለፈው እገሥጻቸዋለሁ። ከእኔ ሸሽተው ሄደዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐምፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ እታደጋቸው ነበር፥ እነርሱ ግን ሐሰትን ተናገሩብኝ። በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፤ በእኔም ላይ ዓመፁ። ክንዳቸውን ያስተማርሁና ያጸናሁ እኔ ነበርሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን አሴሩብኝ። ከንቱ ወደ ሆነው ነገር ተመለሱ፤ እንደ ረገበ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸው ከክፉ አንደበታቸው የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።