ሆሴዕ 7:8-16

ሆሴዕ 7:8-16 NASV

“ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋራ ተደባለቀ፤ ኤፍሬም ያልተገላበጠ ቂጣ ነው። እንግዶች ጕልበቱን በዘበዙ፤ እርሱ ግን አላስተዋለም። ጠጕሩም ሽበት አወጣ፤ እርሱ ግን ልብ አላለም። የእስራኤል ትዕቢት በራሱ ላይ መሰከረበት፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን፣ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም፤ እርሱንም አልፈለገም። “ኤፍሬም በቀላሉ እንደምትታለል፣ አእምሮም እንደሌላት ርግብ ነው፤ አንድ ጊዜ ወደ ግብጽ ይጣራል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ አሦር ይዞራል። ሲበርሩ፣ መረቤን በላያቸው እዘረጋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎችም ጐትቼ አወርዳቸዋለሁ። ስለ ክፉ ሥራቸውም፣ በጉባኤ መካከል እቀጣቸዋለሁ። ወዮ ለእነርሱ፤ ከእኔ ርቀው ሄደዋልና! ጥፋት ይምጣባቸው! በእኔ ላይ ዐምፀዋልና። ልታደጋቸው ፈለግሁ፤ እነርሱ ግን በእኔ ላይ ሐሰት ይናገራሉ። ከልባቸው ወደ እኔ አይጮኹም፤ ነገር ግን በዐልጋቸው ላይ ሆነው ያለቅሳሉ። ስለ እህልና ስለ አዲስ የወይን ጠጅ ይሰበሰባሉ፤ ነገር ግን ከእኔ ዘወር ብለዋል። እኔ አሠለጠንኋቸው፤ አጠነከርኋቸውም፤ እነርሱ ግን ዐደሙብኝ። ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፤ ዒላማውን እንደ ሳተ ቀስት ናቸው፤ መሪዎቻቸው ስለ ክፉ ቃላቸው፣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በዚህም ምክንያት በግብጽ ምድር፣ መዘባበቻ ይሆናሉ።”