ኦሪት ዘፍጥረት 21:9-19

ኦሪት ዘፍጥረት 21:9-19 መቅካእኤ

ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው። አብርሃምንም “ይህችን ባርያ ከነልጇ አባርራት፥ የዚህች ባርያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና” አለችው። ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው “ስለ ባርያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፥ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ፥ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና። የባርያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ፥ ዘርህ ነውና።” አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፥ እንጀራንም ወሰደ፥ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፥ ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት፥ እርሷም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች። ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፥ ብላቴናውንም ከአንድ ቁጥቋጦ በታች ጣለችው፥ እርሷም ሄደች ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች፥ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ፥ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፦ “አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው፥ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጉድጓድንም አየች፥ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}