ዘፍጥረት 21:9-19

ዘፍጥረት 21:9-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሣራም ግብ​ፃ​ዊቱ አጋር ለአ​ብ​ር​ሃም የወ​ለ​ደ​ች​ለ​ትን ልጅ ይስ​ማ​ኤ​ልን ከል​ጅዋ ከይ​ስ​ሐቅ ጋር ሲጫ​ወት አየ​ችው። ሣራም አብ​ር​ሃ​ምን አለ​ችው፥ “ይህ​ችን ባሪያ ከነ​ል​ጅዋ አባ​ር​ራት፤ የዚ​ህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይ​ስ​ሐቅ ጋር አይ​ወ​ር​ስ​ምና።” ይህም ነገር በአ​ብ​ር​ሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነ​በት። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አብ​ር​ሃ​ምን አለው፥ “ስለ​ዚች አገ​ል​ጋ​ይ​ህና ስለ ሕፃኑ አት​ዘን፤ ሣራም የም​ት​ነ​ግ​ር​ህን ቃል ሁሉ ስማ፤ በይ​ስ​ሐቅ ዘር ይጠ​ራ​ል​ሃ​ልና። የባ​ሪ​ያ​ዪ​ቱን ልጅ ደግሞ ታላቅ ሕዝብ አደ​ር​ገ​ዋ​ለሁ፤ ዘርህ ነውና።” አብ​ር​ሃ​ምም ማልዶ ተነሣ፤ እን​ጀ​ራ​ንም ወሰደ፤ የውኃ አቍ​ማ​ዳ​ንም ለአ​ጋር በት​ከ​ሻዋ አሸ​ከ​ማት፤ ሕፃ​ኑ​ንም ሰጥቶ አስ​ወ​ጣት፤ እር​ስ​ዋም ሄደች፤ በዐ​ዘ​ቅተ መሐ​ላም በኩል ባለው ምድረ በዳ ተቅ​በ​ዘ​በ​ዘች። ውኃ​ውም ከአ​ቍ​ማ​ዳው አለቀ፤ ሕፃ​ኑ​ንም ከአ​ንድ ቍጥ​ቋጦ ሥር ጥላው ሄደች፤ ልጄ ሲሞት አላ​የ​ውም ብላ ቀስት ተወ​ር​ውሮ የሚ​ደ​ር​ስ​በ​ትን ያህል ርቃ በአ​ን​ጻሩ እየ​ተ​መ​ለ​ከ​ተች፥ ፊት ለፊት ተቀ​መ​ጠች፤ ቃል​ዋ​ንም አሰ​ምታ አለ​ቀ​ሰች። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የሕ​ፃ​ኑን ጩኸት ሰማ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መል​አክ ከሰ​ማይ አጋ​ርን እን​ዲህ ሲል ጠራት፥ “አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የል​ጅ​ሽን ድምፅ ባለ​በት ስፍራ ሰም​ቶ​አ​ልና አት​ፍሪ። ተነሺ፤ ልጅ​ሽ​ንም አንሺ፤ በእ​ጅ​ሽም አጽ​ኚው፤ ትልቅ ሕዝብ አደ​ር​ገ​ዋ​ለ​ሁና።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ለአ​ጋር ዐይ​ን​ዋን ከፈ​ተ​ላት፤ የውኃ ጕድ​ጓ​ድ​ንም አየች፤ ሄዳም አቍ​ማ​ዳ​ውን በውኃ ሞላች፤ ልጅ​ዋ​ንም አጠ​ጣ​ችው።

ዘፍጥረት 21:9-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብጻዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል በይሥሐቅ ላይ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤ አብርሃምንም፣ “ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርራት፤ የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይሥሐቅ ጋራ አይወርስምና” አለችው። እስማኤል ልጁ ስለ ሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው። እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ ሐሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይሥሐቅ በኩል ስለ ሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ። የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለ ሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።” በማግስቱም አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሟት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር። በእርኮት የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ፣ ልጁን ከአንድ ቍጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው። ከዚያም፣ “ልጁ ሲሞት ዐይኔ አያይም” ብላ፣ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ዐረፍ አለች፤ እርሷም እየተንሰቀሰቀች ታለቅስ ጀመር። እግዚአብሔርም የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ። ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጕድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች።

ዘፍጥረት 21:9-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው። አብርህምንም፤ ይህችን ባሪያ ከነልጅዋ አሳድድ የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና አለችው። ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው ስለ ባሪያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፤ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና። የባሪያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ ዘርህ ነውና። አብርሃምም ማልዶ ተነሣ እንጀራንም ወሰደ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትክሻው አሸከማት ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት እርስዋም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቀበዘበዘች። ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፤ ብላቴናውንም ከአንድ ቍጥቋጦ በታች ጣለችው እርስዋም ሄደች፥ ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፥ አጋር ሆይ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና። እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት የውኃ ጕድጓድንም አየች ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች ብላቴናውንም አጠጣች።

ዘፍጥረት 21:9-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ግብጻዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል ከዕለታት አንድ ቀን ሣራ ከልጅዋ ከይስሐቅ ጋር ሲጫወት አየችው፤ ሣራም አብርሃምን “ይህችን አገልጋይ ከነልጅዋ ወዲያ አባርልኝ፤ የዚህች አገልጋይ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አብሮ መውረስ አይገባውም” አለችው። አብርሃምም ስለ ልጁ ስለ እስማኤል በብርቱ ተጨነቀ፤ እግዚአብሔር ግን አብርሃምን “ስለ ልጁና ስለ አገልጋይቱ ስለ አጋር አትጨነቅ፤ ዘር የሚወጣልህ በይስሐቅ በኩል ስለ ሆነ ሣራ የምትልህን ሁሉ አድርግ፤ የአገልጋይቱም ልጅ የአንተ ልጅ ስለ ሆነ ታላቅ ሕዝብ እስኪሆን ድረስ ዘሩን አበዛለሁ” አለው። በማግስቱ ጠዋት አብርሃም በማለዳ ተነሣ፤ ጥቂት ምግብ፥ ውሃም በአቁማዳ ሞልቶ ለአጋር ሰጣት፤ ልጁንም በጀርባዋ አሳዝሎ ከቤት አስወጣት፤ እርስዋም ከዚያ ወጥታ በቤርሳቤህ በረሓ ትንከራተት ጀመር። በአቁማዳ የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ ልጁን በቊጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው፤ እርስዋም “ልጄ ሲሞት ማየት አልፈልግም” በማለት ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያኽል ርቃ ተቀመጠች፤ እዚያም ሆና ታለቅስ ጀመር። እግዚአብሔርም ልጁ ምርር ብሎ ሲያለቅስ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን “አጋር ሆይ፤ የምትጨነቂበት ነገር ምንድን ነው? እግዚአብሔር የልጁን ለቅሶ ሰምቶአልና አይዞሽ አትፍሪ፤ ተነሺ፤ ሂጂና ልጁን አንሥተሽ ዕቀፊው የእርሱንም ዘር አበዛለሁ፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ” አላት። በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ዐይኖችዋን ከፈተላትና አንድ የውሃ ጒድጓድ አየች፤ ሄዳም በአቁማዳው ውሃ ሞላች፤ ለልጅዋም አጠጣችው።

ዘፍጥረት 21:9-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው። አብርሃምንም “ይህችን ባርያ ከነልጇ አባርራት፥ የዚህች ባርያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና” አለችው። ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው “ስለ ባርያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፥ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ፥ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና። የባርያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ፥ ዘርህ ነውና።” አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፥ እንጀራንም ወሰደ፥ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፥ ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት፥ እርሷም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች። ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፥ ብላቴናውንም ከአንድ ቁጥቋጦ በታች ጣለችው፥ እርሷም ሄደች ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች፥ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ፥ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፦ “አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው፥ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጉድጓድንም አየች፥ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች።