ኦሪት ዘፍጥረት 21:9-19
ኦሪት ዘፍጥረት 21:9-19 አማ05
ግብጻዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል ከዕለታት አንድ ቀን ሣራ ከልጅዋ ከይስሐቅ ጋር ሲጫወት አየችው፤ ሣራም አብርሃምን “ይህችን አገልጋይ ከነልጅዋ ወዲያ አባርልኝ፤ የዚህች አገልጋይ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አብሮ መውረስ አይገባውም” አለችው። አብርሃምም ስለ ልጁ ስለ እስማኤል በብርቱ ተጨነቀ፤ እግዚአብሔር ግን አብርሃምን “ስለ ልጁና ስለ አገልጋይቱ ስለ አጋር አትጨነቅ፤ ዘር የሚወጣልህ በይስሐቅ በኩል ስለ ሆነ ሣራ የምትልህን ሁሉ አድርግ፤ የአገልጋይቱም ልጅ የአንተ ልጅ ስለ ሆነ ታላቅ ሕዝብ እስኪሆን ድረስ ዘሩን አበዛለሁ” አለው። በማግስቱ ጠዋት አብርሃም በማለዳ ተነሣ፤ ጥቂት ምግብ፥ ውሃም በአቁማዳ ሞልቶ ለአጋር ሰጣት፤ ልጁንም በጀርባዋ አሳዝሎ ከቤት አስወጣት፤ እርስዋም ከዚያ ወጥታ በቤርሳቤህ በረሓ ትንከራተት ጀመር። በአቁማዳ የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ ልጁን በቊጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው፤ እርስዋም “ልጄ ሲሞት ማየት አልፈልግም” በማለት ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያኽል ርቃ ተቀመጠች፤ እዚያም ሆና ታለቅስ ጀመር። እግዚአብሔርም ልጁ ምርር ብሎ ሲያለቅስ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን “አጋር ሆይ፤ የምትጨነቂበት ነገር ምንድን ነው? እግዚአብሔር የልጁን ለቅሶ ሰምቶአልና አይዞሽ አትፍሪ፤ ተነሺ፤ ሂጂና ልጁን አንሥተሽ ዕቀፊው የእርሱንም ዘር አበዛለሁ፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ” አላት። በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ዐይኖችዋን ከፈተላትና አንድ የውሃ ጒድጓድ አየች፤ ሄዳም በአቁማዳው ውሃ ሞላች፤ ለልጅዋም አጠጣችው።

