ኦሪት ዘፀአት 15:1-18

ኦሪት ዘፀአት 15:1-18 መቅካእኤ

በዚያን ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለጌታ ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ “ለጌታ እዘምራለሁ በክብር ከፍ ከፍ ብሏልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጌታ ኃይሌና መዝሙሬ ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነዋለሁም፥ የአባቴ አምላክ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። ጌታ ተዋጊ ነው፥ ስሙም ጌታ ነው፤ የፈርዖንን ሰረገሎችና ሠራዊቱን በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት መኮንኖችም በቀይ ባሕር ሰጠሙ። ቀላያትም ከደኑአቸው፤ እንደ ድንጋይ ወደ ባሕር ጥልቀት ወረዱ። ቀኝህ ጌታ ሆይ፥ በኃይል ታላቅ ነው፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጌታ ሆይ፥ ጠላትን አደቀቀ። የግርማህ ታላቅነት አንተን በመቃወም የተነሱብህን ጣላቸው፤ ቁጣህን ሰደድህ፥ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ጥልቁም በባሕር ልብ ውስጥ ረጋ። ጠላትም፦ አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ በእነርሱም ፍላጎቴ ይሞላል፥ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። ትንፋሽህን እፍ አልክባቸው፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ ብረት ሰጠሙ። ከአማልክት መካከል ጌታ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በቅድስና ባለግርማ፥ በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። በታማኝ ኪዳንህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራሃቸው፤ በኃይልህ ወደ ቅድስናህ ማደሪያ አስገባሃቸው። ሕዝቦች ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ፍርሃት ያዛቸው። የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞዓብ መሪዎች መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ ጌታ ሆይ የገዛኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ በኃይልህ ታላቅነት፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፥ እንደ ድንጋይ ቀጥ አሉ። አንተ ታመጣቸዋለህ፥ በርስትህም ተራራ ትተክላቸዋለህ፥ ጌታ ሆይ ለማደሪያህ በሠራኸው ስፍራ፥ ጌታ ሆይ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ። ጌታ ለዘለዓለም ዓለም ይነግሣል።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}