ዘፀአት 15:1-18
ዘፀአት 15:1-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያ ጊዜም ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ “ለእግዚአብሔር እንዘምራለን፤ በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። እኔን ለማዳን ረዳትና ሰዋሪ ሆነኝ፤ ይህ አምላኬ ነው፤ አመሰግነውማለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው፤ ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ጦርነትን ያጠፋል፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው፤ የፈርዖንን ሰረገሎች፥ ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው። በሦስት የተከፈሉ ፈረሰኞችም በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ። ማዕበልም ከደናቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ። አቤቱ፥ ቀኝህ በኀይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቶችን አደቀቀ። በክብርህም ብዛት ጠላቶችህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰደድህ፤ እንደ ገለባም በላቸው። በቍጣህ እስትንፋስ ውኃው ቆመ፤ ውኃዎች እንደ ግደግዳ ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር መካከል ረጋ። ጠላትም፦ ‘አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፤ ምርኮም እካፈላለሁ፤ ነፍሴንም አጠግባታለሁ፤ በሰይፌም እገድላለሁ፤ በእጄም እገዛለሁ’ አለ። ነፋስህን ላክህ፤ ባሕርም ከደናቸው፤ በብዙ ውኆች ውስጥ እንደ አረር ሰጠሙ። አቤቱ፦ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማን ነው? በምስጋና የተደነቅህ ነህ፤ ድንቅንም የምታደርግ ነህ፤ ቀኝህን ዘረጋህ፤ ምድርም ዋጠቻቸው። በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኀይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ ጠራሃቸው። አሕዛብ ሰሙ፤ ተቈጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው። ያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ሸሹ፤ የሞዓብንም አለቆች መንቀጠቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። ፍርሀትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ የክንድህ ብርታትም ከድንጋይ ይልቅ ጸና፤ አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፥ የተቤዠሃቸው እኒህ ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፤ አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፤ በመመስገኛህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፤ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለምም ይነግሣል።
ዘፀአት 15:1-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ሙሴና እስራኤላውያን ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ “ከፍ ከፍ ብሎ ከብሯልና፣ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣ በባሕር ውስጥ ጥሏልና። “እግዚአብሔር ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤ ድነቴም ሆነልኝ፤ እርሱ አምላኬ ነው፤ አመሰግነዋለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው፤ እኔም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው። የፈርዖንን ሠረገሎችና ሰራዊት፣ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ ምርጥ የሆኑት የፈርዖን ሹማምት፣ ቀይ ባሕር ውስጥ ሰጠሙ። ቀላያትንም ለበሱ፤ እንደ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ወረዱ። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ቀኝ እጅህ በግርማ ከበረ፤ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ቀኝ እጅህ ጠላትን አደቀቀ። “በግርማህ ታላቅነት፣ የተቃወሙህን ጣልሃቸው፤ ቍጣህን ሰደድህ፤ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ፣ ውሆች ተቈለሉ፤ ፈሳሾችም እንደ ግድግዳ ቆሙ፤ የጥልቁ ውሃ ባሕሩ ውስጥ ረጋ። ጠላት፣ ‘አሳድዳቸዋለሁ፤ እማርካቸዋለሁ፤ ምርኮን እካፈላለሁ፤ ነፍሴ በእነርሱ ትጠግባለች፤ ሰይፌን እመዝዛለሁ፤ እጄም ትደመስሳቸዋለች አለ።’ አንተ ግን እስትንፋስህን አነፈስህ፤ ባሕርም ከደናቸው፤ በኀያላን ውሆች፣ እንደ ብረት ሰጠሙ። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ? በቅድስናው የከበረ፣ በክብሩ የሚያስፈራ፣ ድንቆችን የሚያደርግ፣ እንደ አንተ ማን አለ? “ቀኝ እጅህን ዘረጋህ፤ ምድርም ዋጠቻቸው። በማይለወጠው ፍቅርህ፣ የተቤዠሃቸው ሕዝብህን ትመራለህ፤ እነርሱን በብርታትህ፣ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ ትመራቸዋለህ። አሕዛብ ይሰማሉ፤ ይንቀጠቀጡማል፤ የፍልስጥኤምን ሕዝብ ሥቃይ ይይዛቸዋል። የኤዶምም አለቆች ይርዳሉ፤ የሞዓብ አለቆች በእንቅጥቃጤ ይያዛሉ፤ የከነዓን ሕዝብ ይቀልጣሉ። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህ እስከሚያልፉ ድረስ፣ የተቤዠሃቸው ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፣ ድንጋጤና ሽብር በእነርሱ ላይ ይመጣል፤ በክንድህ ብርታት፣ እንደ ድንጋይ የማይንቀሳቀሱ ይሆናሉ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማደሪያህ እንዲሆን በሠራኸው ስፍራ፣ ጌታ ሆይ፤ እጆችህ በሠሩት መቅደስ፣ በርስትህ ተራራ ላይ፣ ታመጣቸዋለህ፤ ትተክላቸዋለህም። “እግዚአብሔር፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”
ዘፀአት 15:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፤ “በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጉልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፤ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው፤ የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ። ቀላያትም ከደኑአቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ። አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ። በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰድደህ፤ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፤ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ። ጠላትም፥ ‘አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፤ ምርኮም እካፈላለሁ፤ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፤ እጄም ታጠፋቸዋለች’ አለ። ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ። አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው። አሕዛብ ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው። የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞአብን ኃያላን መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ በክንድህ ብርታት እንደ ድንጋይ ዝም አሉ። አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፥ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፥ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ። እግዚአብሔር ለዘላለሙ እስከ ፍጻሜ ይነግሣል።
ዘፀአት 15:1-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ሙሴና የእስራኤል ሕዝብ ከዚህ የሚከተለውን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፦ “ፈረሱንና ፈረሰኛውን ወደ ባሕር በመጣል፥ ክብር የተሞላው ድል ስለ ተጐናጸፈ፥ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ። እግዚአብሔር በመዝሙር የማመሰግነው መከላከያ ኀይሌ ነው፤ ከጠላት እጅ ያዳነኝ ታዳጊዬም እርሱ ነው፤ እርሱ አምላኬ ስለ ሆነ አመሰግነዋለሁ፤ የአባቴም አምላክ ስለ ሆነ፥ ስለ ገናናነቱ እዘምራለሁ። እግዚአብሔር ብርቱ ጦረኛ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው። “የንጉሡን ሠራዊት ከነሠረገላው ወደ ባሕር ጣለ፤ ምርጥ የሆኑት የጦር አዛዦች በቀይ ባሕር ውስጥ ሰጥመው ቀሩ። ጥልቁ ባሕር አሰጠማቸው፤ እንደ ድንጋይም አቈልቊለው ወደ ባሕሩ ጥልቀት ወረዱ። “አምላክ ሆይ፥ የቀኝ እጅህ ኀይል፥ ባለ ግርማ ነው፤ ጠላትን ሰባብሮ ይጥላል፤ ግርማ በተሞላው ድል አድራጊነትህ ጠላትህን ገለበጥህ፤ ቊጣህ እንደ እሳት ስለ ነደደ እንደ ገለባ በላቸው። በቊጣህ እስትንፋስ፥ ውሃው ወደ ላይ ተቈለለ፤ እንደ ግድግዳም ቀጥ ብሎ ቆመ፤ በጥልቅ ስፍራ ያለውም ውሃ፥ ረግቶ ጠጠረ። ‘ጠላትማ አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፤ ሀብታቸውንም እካፈላለሁ፤ የፈለግኹትንም እወስዳለሁ፤ ሰይፌንም መዝዤ አጠፋቸዋለሁ’ ብሎ ነበር፤ ነገር ግን አምላክ ሆይ፥ ከአንተ በተገኘው በአንድ ትንፋሽ ግብጻውያን ሁሉ ሰጠሙ፤ በጥልቅ ባሕር ውስጥ እንደ ተጣለ ብረት ሆነው ቀሩ። “አምላክ ሆይ፥ ከአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅድስናስ እንደ አንተ ያለ ባለግርማ ማን ነው? አንተ ያደረግሃቸውን ተአምራትና አስገራሚ ሥራዎች ሊያደርግ የሚችልስ ማን አለ? ቀኝ እጅህን በዘረጋህ ጊዜ ጠላቶቻችንን ምድር ዋጠቻቸው፤ በማይለወጥ ፍቅርህ ያዳንካቸውን ሕዝብ መራህ፤ በብርታትህም ወደ ተቀደሰችው ምድር እንዲገቡ አደረግህ፤ አሕዛብ ሁሉ ይህን ሰምተው በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ ፍልስጥኤማውያንም ተሸበሩ፤ የኤዶም መሪዎች ተስፋ ቈረጡ፤ የሞአብም ኀያላን ተንቀጠቀጡ፤ የከነዓንም ሕዝብ ወኔ ከዳቸው። አምላክ ሆይ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ ፍርሀትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ በሥልጣንህ እንደ ድንጋይ ጸጥ አሉ። አምላክ ሆይ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ፥ ወገኖችህን አንተ ታስገባቸዋለህ፤ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ። እግዚአብሔር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል።
ዘፀአት 15:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያን ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለጌታ ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ፦ “ለጌታ እዘምራለሁ በክብር ከፍ ከፍ ብሏልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጌታ ኃይሌና መዝሙሬ ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነዋለሁም፥ የአባቴ አምላክ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። ጌታ ተዋጊ ነው፥ ስሙም ጌታ ነው፤ የፈርዖንን ሰረገሎችና ሠራዊቱን በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት መኮንኖችም በቀይ ባሕር ሰጠሙ። ቀላያትም ከደኑአቸው፤ እንደ ድንጋይ ወደ ባሕር ጥልቀት ወረዱ። ቀኝህ ጌታ ሆይ፥ በኃይል ታላቅ ነው፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጌታ ሆይ፥ ጠላትን አደቀቀ። የግርማህ ታላቅነት አንተን በመቃወም የተነሱብህን ጣላቸው፤ ቁጣህን ሰደድህ፥ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ጥልቁም በባሕር ልብ ውስጥ ረጋ። ጠላትም፦ አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ በእነርሱም ፍላጎቴ ይሞላል፥ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። ትንፋሽህን እፍ አልክባቸው፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ ብረት ሰጠሙ። ከአማልክት መካከል ጌታ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በቅድስና ባለግርማ፥ በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው። በታማኝ ኪዳንህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራሃቸው፤ በኃይልህ ወደ ቅድስናህ ማደሪያ አስገባሃቸው። ሕዝቦች ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ፍርሃት ያዛቸው። የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞዓብ መሪዎች መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ። ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ ጌታ ሆይ የገዛኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ በኃይልህ ታላቅነት፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፥ እንደ ድንጋይ ቀጥ አሉ። አንተ ታመጣቸዋለህ፥ በርስትህም ተራራ ትተክላቸዋለህ፥ ጌታ ሆይ ለማደሪያህ በሠራኸው ስፍራ፥ ጌታ ሆይ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ። ጌታ ለዘለዓለም ዓለም ይነግሣል።”