ዘፀአት 15:1-18

ዘፀአት 15:1-18 NASV

ከዚያም ሙሴና እስራኤላውያን ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ “ከፍ ከፍ ብሎ ከብሯልና፣ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣ በባሕር ውስጥ ጥሏልና። “እግዚአብሔር ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤ ድነቴም ሆነልኝ፤ እርሱ አምላኬ ነው፤ አመሰግነዋለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው፤ እኔም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው። የፈርዖንን ሠረገሎችና ሰራዊት፣ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ ምርጥ የሆኑት የፈርዖን ሹማምት፣ ቀይ ባሕር ውስጥ ሰጠሙ። ቀላያትንም ለበሱ፤ እንደ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ወረዱ። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ቀኝ እጅህ በግርማ ከበረ፤ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ቀኝ እጅህ ጠላትን አደቀቀ። “በግርማህ ታላቅነት፣ የተቃወሙህን ጣልሃቸው፤ ቍጣህን ሰደድህ፤ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ፣ ውሆች ተቈለሉ፤ ፈሳሾችም እንደ ግድግዳ ቆሙ፤ የጥልቁ ውሃ ባሕሩ ውስጥ ረጋ። ጠላት፣ ‘አሳድዳቸዋለሁ፤ እማርካቸዋለሁ፤ ምርኮን እካፈላለሁ፤ ነፍሴ በእነርሱ ትጠግባለች፤ ሰይፌን እመዝዛለሁ፤ እጄም ትደመስሳቸዋለች አለ።’ አንተ ግን እስትንፋስህን አነፈስህ፤ ባሕርም ከደናቸው፤ በኀያላን ውሆች፣ እንደ ብረት ሰጠሙ። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ? በቅድስናው የከበረ፣ በክብሩ የሚያስፈራ፣ ድንቆችን የሚያደርግ፣ እንደ አንተ ማን አለ? “ቀኝ እጅህን ዘረጋህ፤ ምድርም ዋጠቻቸው። በማይለወጠው ፍቅርህ፣ የተቤዠሃቸው ሕዝብህን ትመራለህ፤ እነርሱን በብርታትህ፣ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ ትመራቸዋለህ። አሕዛብ ይሰማሉ፤ ይንቀጠቀጡማል፤ የፍልስጥኤምን ሕዝብ ሥቃይ ይይዛቸዋል። የኤዶምም አለቆች ይርዳሉ፤ የሞዓብ አለቆች በእንቅጥቃጤ ይያዛሉ፤ የከነዓን ሕዝብ ይቀልጣሉ። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህ እስከሚያልፉ ድረስ፣ የተቤዠሃቸው ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፣ ድንጋጤና ሽብር በእነርሱ ላይ ይመጣል፤ በክንድህ ብርታት፣ እንደ ድንጋይ የማይንቀሳቀሱ ይሆናሉ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ማደሪያህ እንዲሆን በሠራኸው ስፍራ፣ ጌታ ሆይ፤ እጆችህ በሠሩት መቅደስ፣ በርስትህ ተራራ ላይ፣ ታመጣቸዋለህ፤ ትተክላቸዋለህም። “እግዚአብሔር፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}