መጽሐፈ ባሮክ 3

3
1የእስራኤል አምላክ ሁሉን ቻይ ጌታ ሆይ! በጭንቅ የተያዘች ነፍስና በድካም የተጨነቀ መንፈስ ወዳንተ ይጣራሉ፤ 2ጌታ ሆይ ስማ፥ ይቅርም በለን፥ በአንተ ፊት በድለናልና፤ 3አንተ ለዘለዓለም የምትነግሥ ነህ፤ እኛም ለዘለዓለሙ የምንጠፋ ነን። 4የእስራኤል አምላክ ሁሉን ቻይ ጌታ ሆይ! የእስራኤልን ሙታን፥ በፊትህ የበደሉ ሰዎች የልጆቻቸውን ጸሎታቸውን ስማ፤ የአምላካቸውን የጌታን ቃል አልሰሙም፥ ስለዚህ መቅሰፍቶች ተጣበቁብን። 5የአባቶቻችን ክፋት አታስታውስ፤ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ኃይልህንና ስምህን አስታውስ። 6አንተ ጌታ አምላካችን ነህና፥ ጌታ ሆይ የምናመሰግነውም አንተን ነው። 7ስለዚህም ነው ስምህን እንድንጠራ አንተን መፍራት በልባችን ውስጥ ያሳደርኸው፤ በስደት ላይ ሆነን እናመስግንሃለን፥ በአንተ ላይ የበደሉትን የአባቶቻችንን ክፋት ሁሉ ከልባችን አርቀናልና። 8ጌታ አምላካችን በተውት በአባቶቻችን ክፋት ምክንያት ስድብ፥ እርግማንና ቅጣት ሆነን እነሆ እኛ ዛሬ አንተ በበተንኸን በምርኮ ላይ ነን።
ጥበብ፥ የእስራኤል ሥልጣን
9 # ምሳ. 4፥20-22። እስራኤል ሆይ የሕይወትን ትእዛዝ ስማ፤ ጆሮን ስጥ፥ ጥበብንም ተማር። 10ለምን እስራኤል ሆይ፥ በጠላት ምድር የተገኘኸው፥ በሰው አገር ያረጀኸው፥ ከሞቱት ጋር የረከስኸው፥ 11በሲኦል ካሉት ጋር የተቆጠርኸው ለምንድን ነው? 12የጥበብን ምንጭ ተውህ። 13በእግዚአብሔር መንገድ ሄደህ ቢሆን ኖሮ ለዘለዓለም በሰላም በኖርህ ነበር። 14ጥበብ የት እንዳለ፥ ኃይል የት እንዳለ፥ ማስተዋል የት እንዳለ ተማር፤ እንዲሁም የዘመን ርዝመት፥ ሕይወት፥ የዐይን ብርሃንና ሰላም የት እንዳለ እንድታውቅ ተማር። 15#ኢዮብ 28፥12፤20።ቦታዋን ማን አገኘ? ወደ መዛግብትዋስ ማን ገባ? 16የአሕዛብ ገዢዎች የት አሉ? የምድር አውሬዎች ጌቶችስ#3፥16 የምድር አውሬዎችን የሚያስተዳድሩ። የት ናቸው? 17በሰማይ ወፎች የሚቀልዱ ሰዎች የት ናቸው? ሰዎች እምነታቸውን የጣሉባቸው ብርና ወርቅ ያከማቹ፥ ሀብቶቻቸው መጠን ያልነበረው እነዚያ ሰዎች የት አሉ? 18ብር የሚያቀልጡና ሐሳቦቻቸው ሁሉ በብር ላይ የነበረ እነዚያ ሰዎች የት ናቸው? ሥራቸው ከሰው ሐሳብ በላይ የነበረ፥ እነዚያ ሰዎች የት ናቸው? 19ሁሉም ጠፍተዋል፥ ወደ ሲኦልም ወርደዋል፥ በእነሱ ፈንታ ሌሎች ተነስተዋል። 20ወጣቶች ብርሃን አይተው በምድር ላይ ኖረዋል፤ የዕውቀትን መንገድ ግን አላወቁም። 21መንገድዋንም አላስተዋሉም፥ አልያዙአትምም፤ ልጆቻቸውም ከመንገድዋ ርቀዋል። 22በከነዓንም አልተሰማችም፤ በቴማንም አልታየችም። 23በምድር ላይ ማስተዋልን የሚፈልጉ የአጋር ልጆች፥ የሜራንና የቴማን ነጋዴዎች፥ የተረት የሚነግሩና ማስተዋልን የሚፈልጉ የጥበብን መንገድ አላወቁም፤ መንገዶቿን አላስታወሱም። 24እስራኤል ሆይ እግዚአብሔር ቤት እንዴት ታላቅ ነው! የግዛቱ መጠን እንዴት ሰፊ ነው፤ 25ትልቅ ነው መጨረሻም የለው፤ ከፍ ያለና የማይለካ ነው። 26#ዘፍ. 6፥4፤ ጥበ. 14፥6።ከጥንት ጀምሮ የታወቁ፥ ቁመታቸው ረጅም የሆነ፥ ጦርነትንም የሚያውቁ፥ ግዙፎቹ የተወለዱት እዚያ ነው። 27እግዚአብሔር እነርሱን አልመረጣቸውም፤ የዕውቀትንም መንገድ አልሰጣቸውም። 28ማስተዋል አልነበራቸውምና ጠፉ፤ በሞኝነታቸው ጠፉ። 29ወደ ሰማይ ሄዶ የወሰዳት፥ ከደመናዎቹም ያወረዳት ማነው? 30ባሕሩን አቋርጦ ሄዶ ያገኛት፥ በተመረጠ ወርቅስ ያመጣት ማነው? 31ወደ እርሷ የሚወስደውን መንገድ ማንም አያውቀውም፥ ወደ እርሷ ስለሚወስደው መንገድም መገንዘብ የሚችል ማንም የለም። 32ነገር ግን ሁሉን ነገር የሚያውቅ ሰው ያውቃታል፥ በማስተዋሉም አገኛት። ምድርን ለዘለዓለም ያዘጋጀ በአራት እግር አራዊት ሞልቷታል፤ 33ብርሃንን ይልካል፥ እርሱም ይሄዳል፤ ይጠራዋል፥ በመንቀጥቀጥም ይታዘዘዋል። 34ከዋክብትም በመጠበቂያቸው ሆነው ያበራሉ፥ ሐሴትም ያደርጋሉ። 35ሲጠራቸው “እዚህ አለን” አሉ፤ ለፈጠራቸውም በደስታ አበሩ። 36አምላካችን ይህ ነው፤ ከእሱ ጋር መወዳደር የሚችል ከቶ የለም። 37የዕውቀትን መንገድ ሁሉ አገኛት። እርሷንም ለአገልጋዩ ለያዕቆብ፥ ለሚወደውም ለእስራኤል ሰጠው። 38ከዚህ በኋላ በምድር ላይ ታየች፤ በሰዎች መካከልም ኖረች።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ