መጽሐፈ ባሮክ 4
4
1 #
ሲራ. 24፥23። ይህች የእግዚአብሔር ትእዛዝ መጽሐፍና ለዘለዓለም የምትኖር ሕግ ነች። አጥብቀው የሚይዟት ሁሉ በሕይወት ይኖራሉ፥ የሚተዉአት ይሞታሉ። 2ያዕቆብ ሆይ ተመለስና ያዛት፤ ወደ ብርሃንዋ ጮራም ሂድ። 3ክብርህን ለሌላ አትስጥ፥ ጥቅምህን ለባዕድ አትስጥ። 4እስራኤል ሆይ እኛ የተባረክን ነን፤ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው ነገር ተገልጦልናልና!
የኢየሩሳሌም ቅሬታዎችና ተስፋዎች
5የእስራኤል መታሰቢያ፥ ሕዝቤ ሆይ በርቱ፤ 6ለአሕዛብ ተሽጣችሁ ነበር ለጥፋት ግን አይደለም፥ ነገር ግን እግዚአብሔርን በማስቆጣታችሁ ለጠላቶቻችሁ ተላልፋችሁ ተሰጥታችሁ ነበር። 7ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት በመሠዋት ፈጣሪያችሁን በጣም አስቆጣችሁት። 8የተንከባከባችሁን ዘላለማዊ አምላክ ረስታችሁታል፥ ያሳደገቻችሁን ኢየሩሳሌምንም አሳዝናችኋል። 9የእግዚአብሔር ቁጣ በእናንተ ላይ ሲመጣ ባየች ጊዜ እንዲህ አለች፦ “የጽዮን ጐረቤቶች ስሙ፥ እግዚአብሔር ጽኑ ኀዘን አምጥቶብኛል፤ 10ዘላለማዊ አምላክ ያመጣባቸውን ወንዶች ልጆቼንና የሴቶች ልጆቼን መማረክ አይቻለሁና። 11በሐሴት አሳደግኋቸው፥ ነገር ግን በልቅሶና በኀዘን ሸኘኋቸው። 12በብዙዎች በተጣልሁት፥ በመበለቷ በእኔ ማንም ደስ አይበለው፤ በልጆቼ ኃጢአት ምክንያት ባዶ ቀርቻለሁ፥ ከእግዚአብሔር ሕግ ርቀዋልና። 13ትእዛዞቹን አላወቁም፤ በእግዚአብሔር ትእዛዛት መንገድ አልተከተሉም፤ በሱ ጽድቅ መሠረት የተማሩትን ተከትለው አልሄዱም። 14የጽዮን ጐረቤቶች ይምጡ፤ ዘላለማዊው ያመጣባቸውን የወንዶች ልጆቼና የሴቶች ልጆቼ መማረክ አስታውሱ። 15የማያፍር፥ ባዕድ ቋንቋ የሚናገር፥ ሽማግሌን የማያከብርና ለሕፃን የማይራራ ሕዝብ ከሩቅ አመጣባቸው። 16የመበለትዋን የተወደዱ ልጆች ነጠቁ፤ ከሴቶች ልጆችዋም ለይተው ብቻዋን አስቀሩአት። 17ነገር ግን እኔ እንዴት ልረዳችሁ እችላለሁ? 18ይህን ክፉ ነገር ያመጣባችሁ እርሱ ከጠላቶቻችሁ እጅ ያወጣችኋልና። 19ሂዱ ልጆቼ ሂዱ፤ እኔ ምድረ በዳ ሆኜ ተትቻለሁና። 20የሰላም ልብሴን አወለቅሁ፥ ለልመናዬም ማቅን ለበስሁ፤ በዘመኔን ሁሉ ወደ ዘላለማዊው እጮሃለሁ። 21ልጆቼ ጽኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ጩኹ፤ ከጠላቶቻችሁ አገዛዝና እጅ ያወጣችኋል። 22እንዲያድናችሁ ተስፋዬን በዘላለማዊ አድርጌአለሁና፥ ከዘላለማዊው አዳኛችሁ ፈጥኖ ስለሚመጣላችሁ ምሕረት፥ ከቅዱሱ ደስታ መጣልኝ። 23እኔ በኀዘንና በልቅሶ ሸኝቻችኋለሁና፥ ነገር ግን እግዚአብሔር በደስታና በሐሤት እናንተን መልሶ ለዘለዓለም ለእኔ ይሰጣችኋል። 24የጽዮን ጎረቤቶች አሁን መማረካችሁን እንዳዩ፥ እንዲሁም ከታላቅ ክብርና ከዘላለማዊው ውበት ጋር ከእግዚአብሔር ወደ እናንተ የሚመጣውን መዳናችሁን ፈጥነው ያያሉ። 25ልጆቼ ከእግዚአብሔር የመጣባችሁን ቁጣ በትዕግሥት ተቀበሉ፤ ጠላቶቻችሁ አሳደድዋችሁ፥ ነገር ግን ውድቀታቸውን በፍጥነት ታያላችሁ፤ አንገታቸውንም ትረግጣላችሁ። 26ለግላጋ ልጆቼ በሻከረው መንገድ ሄዱ፤ እንደ ተዘረፉ መንጋዎች በጠላቶች ተወስደው ነበር። 27ልጆቼ ጽኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ጩሁ፤ ይህን ያመጣባችሁ እርሱ ያስባችኋልና፤ 28ከእግዚአብሔር በፈቃዳችሁ እንደራቃችሁ፥ አሁን ደግሞ እርሱን ለመፈለግ በአስር እጥፍ ተመለሱ። 29እነዚህን መከራዎች በእናንተ ላይ ያመጣባችሁ እርሱ ዘላለማዊ ደስታን ከድኅነታችሁ ጋር ያመጣላችኋል። 30ኢየሩሳሌም ሆይ ጽኚ፥ ስምሽን የሰጠሽ እሱ ያጽናናሻልና። 31መከራ ያጸኑብሽና በውድቀትሽ የተደሰቱ ሰዎች ይጐሰቁላሉ። 32ልጆችሽ ባርያዎች የሆኑባቸው ከተሞች ይጐሰቁላሉ፤ ልጆችሽን የተቀበሉ ከተሞች ይጐሰቁላሉ። 33በውድቀትሽ እንደ ተደሰተች፥ በመጥፋትሽም ሐሤት እንደ አደረገች፥ በራሷ መጥፋት ታዝናለች። 34ደስተኞች ሕዝቦቿን እነጥቃታለሁ፥ ትምክሕቷ ወደ ኀዘን ይለወጥል። 35ከዘላለማዊው እሳት ለብዙ ቀኖች ይመጣባታልና፥ ለብዙ ዘመንም የአጋንንት መኖሪያ ትሆናለችና። 36ኢየሩሳሌም ሆይ ወደ ምሥራቅ ተመልከቺ፥ ከእግዚአብሔር የሚመጣልሽንም ደስታ እዪ፤ 37እነሆ የላክሻቸው ልጆችሽ መጡ፤ በእግዚአብሔር ክብር እየተደሰቱ፥ በቅዱሱ ቃል ከምሥራቅና ከምዕራብ ተሰበሰቡ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ባሮክ 4: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ